Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ 30 የነቢይ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት ፦ | ወልድ ዋሕድ

ሰኔ 30

የነቢይ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት

፦ ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው። ይህም በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው።

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች። ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለርስዋ ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን "አይሆንም ዮሐንስ ይባል" አለች። "ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም" አሏት።

አባቱንም ጠቅሰው "ማን ሊባል ትወዳለህ" አሉት። እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ "ዮሐንስ ይባል" ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም የልዑል ነቢይ እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።

ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሔዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት እንዲገድሉትም ጭፍሮችን ላከ ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋራ እንዲሔዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።

ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና "ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት" አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው። ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት። ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ኖረ።

"የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የዐዋጅ ነጋሪ ድምጽ እነሆ" ብሎ ኢያሳያስ የተናገረለት ይህ ነው። ሚልክያስም ስለርሱ እንዲህ አለ "በፊትህ ጎዳናዬን አስተካክሎ የሚጠርግ መልአክተኛዬን እኔ እሰዳለሁ"።

ራሱ መድኃኒታችንም ስርሱ ሲናገር "ሴቶች ከወለዱአቸው መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጠው የለም" ብሏል። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ በአጠመቀውና የማትዳሠሥ ራሱን በዳሠሠው ጊዜ "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" የሚል የአብን ቃል ሰምቷልና።

ዳግመኛም ክብር ይግባውና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥ አየ። እኛንም መድኃኒታችን እንዲምረንና ይቅር እንዲለን በአማላጅነቱ እያመን መታሰቢያውን እናድርግ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱም እኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።