Get Mystery Box with random crypto!

ልጆቻችሁን ሸጣችሁ ምን ገዛችሁ? (አሌክስ አብርሃም) ብዙ ወላጆችን  እያየሁ እና እየሰማሁ ልቤ | የስብዕና ልህቀት

ልጆቻችሁን ሸጣችሁ ምን ገዛችሁ?
(አሌክስ አብርሃም)

ብዙ ወላጆችን  እያየሁ እና እየሰማሁ ልቤ ያዝናል! በተለይ  ልጆች ላላችሁ ሰዎች ከልቤ  ይህን እላለሁ! በዚች ምድር ላይ ለልጆቻችሁ ከእናተ ውጭ  ከልቡ ፍቅር የሚሰጣቸው፣ የሚያወሩት ጠቀመም አልጠቀመም የሚያዳምጣቸው፣ ከልቡ የሚያቅፉቸው፣ የሚስማቸው ፣  ሲያዝኑ መንፈሳቸውን ከፍ የሚያደርግላቸው ፣የሚያጫውታቸው ፣ከዳዴ እስከአዋቂነት ፣ ከዓለማዊ እስከመንፈሳዊው  ጉዞ መንገድ የሚመራቸው ፣  የሚያስተምራቸው፣ ከዚህ ክፉ ዓለም በፍቅር እና እንክብካቤ የሚጋርዳቸው ከወላጅ ውጭ ሌላ ሰው የለም! ወላጅ ከሆንክ ከሆንሽ እናንተ ብቻ ናችሁ ለልጆቻችሁ ያላችኋቸው! ወላ ዘመድ ወላ አስተማሪ ከእናንተ ቀጥሎ ነው! መቸም ደግሞ  የእናተን ሚና አይተኩም!

በተለይ አባቶች!...(በእናንተ ስለሚብስ) በሜካፕና በ"ላይት" ተብረቅርቀው ራሳቸውን ለገበያ የቀረቡ ሴቶችን የማይረባ ወሬና የወሲብ ስሜት የሚያነሳሳ ዳንስ ፣ ራቁትነት፣ ብልግና ፣ ቆሻሻ ጆክና ሀሜት ፣ ጥቅም የሌለው ጫጫታ ወይም ይሄን የሻገተ ፖለቲካ  ለማየት ቲክቶክ፣ ዮቲዮብ፣ ፌስቡክ ወዘተ ላይ ቀን ከሌት አፍጥጠህ ስትገለፍጥና ስትቋምጥ  ውለህ የምታድር አባት ...የምትከፍለው ተራ ካርድ ወይም የኢንተርኔት ሂሳብ ብቻ እንዳይመስልህ!  የልጆችህን ጊዜ ከፍለህ ቆሻሻ ትገዛለህ! ዱቄት በአመድ ትለውጣለህ!

እነዚህ  ሚሊየን ተመልካች ያላቸው ከንቱዎች ለመመልከት ከአንተ ሌላ ተመልካች የሌላቸው ልጆችህን ፊት ትነሳለህ! ፍቅር ትነሳለህ (እንደዛፍ ውሃ እያጠጣህ ስለተውካቸው ልጆች አደጉ አይባልም) ለልጆችህ እያንዳንዷ ሰዓት እያንዳንዷ ደይቃ የነገ እጣፈንታቸው ናት! በየደይቃው በየቅፅበቱ ነው ልጆች በአካልም በመንፈስም  የሚሰሩት! የረሳሀቸው ልጆችህ መረሳት የሚያመጣው የበታችነት ህመም ተጠቂ ይሆናሉ! ጊዚያቸውን ስትነጥቃቸው ከወላጅ ሊያገኙ የሚገባውን መብትና ፍቅር ትነጥቃቸዋለህ! ዛሬ የራካቸው ልጆች ነገ ይርቁሃል! ነገ በጣም ቅርብ ነው! ከስልክህ ቀና ስትል አድገው ታገኛቸዋለህ! ውድ ጊዜህን እንቅልፍህን ሰላምህን ሰጥተህ ስልክህ ላይ ለምታያቸው   ከነመኖርህ  እንኳን ለማያውቁህ የሶሻል ሚዲያ ርካሽ ነጋዴዎች ስትል ከአንተ ሌላ ማንም የሌላቸውን ልጆችህን ቤተሰብህን ትሸጣለህ! "ሊትራሊ" ልጆችህን ሽጠህ ነው የሆነች ቦዘኔ መቀመጫዋን ስታወዛውዝ  ለማየት በጊዜህ የምትገዛው፤በሆነ ሰው ቀልድ የምትገለፍጠው! በየቤታችሁ ያስገባችሁት ኢንተርኔት አጠቃቀሙ በወግ ካልተቃኘ  ልጆቻችሁን ደርድራችሁ በርካሽ  የምትሸጡበት ጉሊት ነው የሚሆነው!

እስኪ ወላጆች ራሳችሁን  ታዘቡ! ለቲክቶክ የምትሰጡትን ጊዜ ለልጆቻችሁ እየሰጣችሁ ነው? ወይስ ወደዛ ዝም እንዲሉ ቲቪ ወይ የሆነ ነገር ሰጥታችሁ ስልካችሁ ላይ ናችሁ? ለትዳር አጋሮቻችሁስ? ለወላጆቻችሁስ? ከቲክቶክ ፌስቡክ ምናምን ፋታ ብትውስዱ እንኳ አዕምሯችሁ የተሞላው በትርኪ ምርኪ ነውና ለልጆቻችሁ የምትሰጡት ደህና ሃሳብ እንኳን የላችሁም!  ስምህ የልጅህን ስም እየተከተለ እንደውሻ ስለጮኸ አባትነትህ ሙሉ ሆነ ማለት አይደለም! ያለህን ጊዜ ሁሉ ለቤተሰብህ ስጥ ፤የተረፉህን ልቅቃሚ ደይቃዎች ወደሶሻል ሚዲያው ወርውር! በቂ ነው! ልጅህን ቤተሰብህን ሸጠህ ቆሻሻ አትግዛ! በፈጠረህ ለሌሎች የላይክና ቪው ቁጥር ከመሆን ለቤተሰብህ አለኝታ ሁን! ባልታደለች አገር ተፈጥረው ያጡት ስፍር ቁጥር የሌለው ነገር ሳያንስ አንተም ተጨምረህ ልጆችህን የቲም አታድርጋቸው! ቆም ብለህ አስብ ከቤተሰቤ የነጠኩትን ጊዜ ምን ገዛሁበት በል? ምን ገዛህበት? አንችም እናት የሆንሽ  እንደዛው!

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence