Get Mystery Box with random crypto!

“ጅል አይሙት እንዲያጫውት!” ከአሌክስ አብርሀም መፅሀፍ-አልተዘዋወረችም በአገራችን ባህል የዝምታ | የስብዕና ልህቀት

“ጅል አይሙት እንዲያጫውት!”
ከአሌክስ አብርሀም
መፅሀፍ-አልተዘዋወረችም

በአገራችን ባህል የዝምታ ትርጉም ግራ የገባው ነው፡፡ እውነት በአደባባይ ሲደፈጠጥ እያዩ አፍን መሸበብ፤ ግን ደግሞ በስሚ ስሚ ለመጣ አሉባልታ ነፍስን ጭምር መስጠት። ጮኾ የማያወራ፣ ሐሳቡን የማይገልጽ ሕዝብ የሐሜት ጫካ ነው። በየጋራና ሸንተረሩ ጥይት ከማስጮኸ የበለጠ፣ ጮኽ ብሎ ያመኑበትን መናገር የሚከብደው ሕዝብ ጀግንነቱ ከባድ ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ በዝም አይነቅዝም ብሒል የነቀዘ ሕይወት እንመራ ዘንድ የፈቀድን ሕዝቦች መሆናችን ሳያንስ ይኽንንም ባህል አድርገን ልንኮራበት ይዳዳናል፡፡

ይኼ ተወልጄ ያደግሁበት ሕዝብ በሹክሹክታ ያወራል፣ ጓዳ ለጓዳ ያወራል፣ እውነት ይሁን ውሸት አግበስብሶ ያወራል፣ እንደ ወረርሽኝ ወሬ በብርሃን ፍጥነት ያዛምታል፣ በአደባባይ ግን ዝምተኛን ያደንቃል- ያበረታታል፡፡ በተረቱ “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” እያለ  ዝንብ ፈርቶ ዝም (እንዴት _ ለዝንብ ዝም ይባላል? ለምን ሰፈራችሁን አጽድታችሁ እንደልባችሁ አታወሩም? የሚል የማሪያም ጠላት ነው!) መንግሥትን ፈርቶ ዝም (እንዴት ዝም በሉ ለሚል መንግሥት ዝም ይባላል አፋኝ መንግሥት እጁን ከአፋችን ላይ እንዲያነሳ መንገር የለብንም ወይ? የሚል የአገር ጠላት ነው) ይሉኝታን ፈርቶ ዝም (እንዴት በይሉኝታ እንለቅ? ብንል የባህል ጠላት መባል ይመጣል፡፡)


ሁሉም ስሕተትና ፍርኃታችን እንደ ትልቅ ሐብት በእሳት ሰይፍ ተከቦ የሚጠበቅ ቅርስ ነው፤ እውነት ብቻ ነው ራቁት፡፡ ለዚያም ሳይሆን አይቀርም እውነት የእብዶችና ሰካራሞች ልፈፋ ተደርጋ በየመድረኩ የምትሳለው፡፡ እብዶች እውነቱን እንዲናገሩለት “ጤነኛው' ከፍሎ ይታደማል፡፡ ይኼ ባህላችን ሲሆን ከያኒ የነፍሱን ጥሪ ጥሎ የጅሎች አፈቀላጤ ይሆናል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ ምክንያት ፍርኃታችን ቢሆንም፣ ይኼንንም በሰበብ ስንጀቡነው (መቼም ሰበብ አናጣ) “ዝምታችን ትዕግስት የወለደው፤ ትዕግስታችንም አምላካችንን የምንፈራ ሕዝቦች ስለሆንን የተጎናጸፍነው ጸጋ ነው” እንላለን፡፡ እውነታው ግን አምላክን መፍራታችን ሳይሆን ፍርኃትን ማምለካችን ነው።

በዚህ ሁሉ ዝምታ ውስጥ የታቀፈ ጅልነት ድርጊት ሆኖ ሲፈለፈል ከግለሰብ እስከ አገር ስንት የጨነገፈ ኑሮ ፈጠረ!? ታዲያ የራሳችን ዝምታ ተጠራቅሞ ሲከብደንና አላራምድ ሲለን፤ በየዘመኑ ጊዜና ሁኔታ እየጠበቅን በጋራ እንጮኻለን። የጨረባ ተዝካር! ይኼን ዓይነቱን ጩኸት አብዮት እንለዋለን (የታዘዙትን ሁሉ እሺ! እያሉ አብዮት አለ ወይ?!) ነገሩ ልክ ውሃ ውስጥ የተነከረ ውሻ፣ ውሃውን ከላዩ ላይ ለማራገፍ በደመነፍስ እንደሚርገፈገፈው ዓይነት ነው፤ ውሃው ቢራገፍም ውሻው ያው ውሻ ነው፡፡ አጯጯኻችን በአንድ ላይ በየአፋችን ስለሆነ ማንም ማንንም አይሰማም፤ ማንም የማይሰማው ጩኸት ደግሞ ከዝምታ እኩል ነው፡፡

ይኼ ዝምታ፣ የጅል ባንዲራ እንጂ ጨዋነት አይደለም። ባንዲራችን ከፍ ብሎ የሚውለበለበው ለዘመናት በተከመረና በደደረ ጅልነታችን ላይ ይመስለኛል፡፡ የባንዲራችንን ቀለም እየጠቀስን የማንሰጠው ትርጉም የለም። ሁሉንም ቀለም እንደ ዳማከሴ ጨቅጭቀን ብንጨምቀው ከጀግንነታችንም በፊት፣ ከኩሩነታችንም በፊት፣ከአገር ፍቅራችንም በፊት የሚንጠባጠበው ጅልነታችን ሳይሆን ይቀራል?!

እሱን እየተቀባን ስንት ጊዜ ከዘመን በሽታ ተፈወስን ብለናል?! ፈውሳችን ሐሰት ነበርና ምስክርነታችን የታተመበት ቀለም ሳይደርቅ፣ ብዙዎች በነጠላም በጅምላም የጅል በትር ሰለባ ሆነው ወደ መቃብር ወርደዋል፡፡


የተረፍነው እንዴት ተረፍን? እያልኩ ሳስብ፣ አንዳንዶች “ምሕረቱ በዝቶልን'' ቢሉም እኔ ግን ፈጣሪም ከዚህች ከኛ ምድር በተዋሰው ተረት “ጅል አይሙት እንዲያጫውት!” ብሎ ለአጫዋችነት ትቶን ይሆናል እላለሁ፡፡ አገሬ ጨዋታና ተጨዋች ይበዛታል፡፡ እንደ አገር ልጅነታችንን አልጨረስንም ይሆን? እስከምል ድረስ የአገሬ ጨዋታ ወዳድነት ያስደምመኛል፡፡

ጅልነቴ ከሕዝብ ባሕር የተቀዳ ነው ስል፣ ለጥፋቴ ሌላ የሕዝብ ክንብንብ ውስጥ መደበቄ አይደለም፤ ምንስ ቢሆን ሕዝብ የሚባለው አጀብ ለሚሊዮኖች ቢሰነጣጠር አንዱ ስንጣሪ መሆኔ አይቀር፡፡ ሕዝባዊ ጀግንነት፤ ሕዝባዊ ታሪክ እንዳለ ሁሉ ከየቤታችን አዋጥተን አገራዊ ያደረግነው ሕዝባዊ ጅልነት አለመኖሩን ማን አጥንቶ ነገረን?! ጅልነት ቀለም ነው፤ ታሪካችን እኛም በግልና በጅምላ አማርን ብለን የተቀባነው የተኳኳልነዉ ጠይም ቀለም፡፡ በዚህ ጠይምነት በኩል ስለተገለጠ ግለሰባዊ ጅልነቴ በጸጸት አወራለሁ... በጓዳዬ ለአገር ያዋጣሁት የጅልነት ድርሻ... ይኽም ከንስሓ ይቆጠር እንደሆን እንጃ፡፡

@zephilosophy
@zephilosophy