Get Mystery Box with random crypto!

፨ሉቃስ ቴዎፍሎስ ለሚባለው ጓደኛው የጻፋለት ደብዳቤ እንጂ ወንጌል አይደለም፥ ለጓደኛው የጻፈው ደግ | ☀ሁዳ መልቲሚዲያ |HUDA MULTIMEDIA

፨ሉቃስ ቴዎፍሎስ ለሚባለው ጓደኛው የጻፋለት ደብዳቤ እንጂ ወንጌል አይደለም፥ ለጓደኛው የጻፈው ደግሞ ጓደኛው ስለ ተማረው ቃል እርግጡን እንዲያውቅ መልካም ሆኖ ስለታየው እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ አይደለም።
፨ማቴዎስ ደግሞ በ 50 ድኅረ ልደት ለዕብራውያን በዕብራይስጥ ደብዳቤ ጽፎ ሳለ ይህ ደብዳቤ ሲጠፋ በማቴዎስ ስም ማንነቱ የማይታወቅ ሰው የማርቆስን ትርክት መሠረት አድርጎ የማቴዎስ ወንጌልን አዘጋጀ።
፨የዮሐንስን ወንጌል የጻፈው ሽማግሌ ዮሐንስ"John the Presbyter" ሲሆን ከሐዋርያው ዮሐንስ ይለያል።
፨ሉቃስ እና ማርቆስ ደግሞ የጳውሎስ ጓደኞች ናቸው እንጂ የኢየሱስ ሐዋርያት አይደለም።

ሆነም ቀረ የመጀመሪያዎቹ የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ፣ የዮሐንስ ወንጌላት ጠፍተዋል፥ ከአንዱ አምላክ ለኢየሱስ የተሰጠው ወንጌል አንድ ሆኖ ሳለ የኢየሱስን ወንጌል ከሠራው ተአምር ጋር ታሪክን ብዙዎች ሲያዘጋጁ ወደ 47 የሚደርሱ ወንጌላት ደርሰው ነበር።
ከእነዚህ ወንጌላት ሄለናዊ ክርስትና"hellenistic christianity" ስለ ህማማት(ስቅለት እና ግድለት) የሚናገረው አራት ወንጌላት መርጦ ሌሎችን ወንጌላት ሳይቀበል ቀርቷል፥ እነዚህ አራት ወንጌላት ከመጻፋቸው በፊት አንድ ወንጌል እንደነበረ እና ያ ወንጌል እንደጠፋ ምሁራን እንዳስቀመጡ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የአዲስ ኪዳን መግቢያ ላይ ተቀምጧል።
ስለዚህ ሄለናዊ ክርስትና ከአሏህ ዘንድ ለዒሣ በተሰጠው ኢንጂል ላይ ታሪክን በመጨመር "ከአሏህ የሆነ ግልጠተ መለኮት ነው" ብለው ዋሽተዋል፦
2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ
3፥71 «የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! እውነቱን በሐሰት ለምን ትቀላቅላላችሁ? እውነቱንም እናንተ የምታውቁ ስትኾኑ ለምን ትደብቃላችሁ?» يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لِمَ تَلْبِسُونَ الْحَقَّ بِالْبَاطِلِ وَتَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ

"እውነቱን በሐሰት ለምን ትቀላቅላላችሁ" የሚለው ይሰመርበት! ሄለናዊ ክርስትና ከአሏህ ዘንድ ለዒሣ በተሰጠው ኢንጂል ላይ ታሪክን መጨመር ብቻ ሳይሆን ከተሰጠው ኢንጂል ላይ እውነትን በመደበቅ ቀንሰዋል፥ ከተቀነሱት መካከል ስለ ነቢያችን"ﷺ" መምጣት የሚናገረው የምስራች ነው፦
7፥157 ለእነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራት እና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍ እና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልእክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት በእርግጥ እጽፍለታለሁ፡፡ الَّذِينَ يَتَّبِعُونَ الرَّسُولَ النَّبِيَّ الْأُمِّيَّ الَّذِي يَجِدُونَهُ مَكْتُوبًا عِندَهُمْ فِي التَّوْرَاةِ وَالْإِنجِيلِ
61፥6 የመርየም ልጅ ዒሣም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥ እና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልእክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደ እናንተ የተላክሁ የአላህ መልእክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ قَالَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ يَا بَنِي إِسْرَائِيلَ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُم مُّصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيَّ مِنَ التَّوْرَاةِ وَمُبَشِّرًا بِرَسُولٍ يَأْتِي مِن بَعْدِي اسْمُهُ أَحْمَدُ

"የማበስር" የሚለው ይሰመርበት! "ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልእክተኛ ስሙ አሕመድ" የሚለው የምስራች አራቱ ወንጌላት ላይ ከሌለ እንግዲያውስ አምላካችን አሏህ ኢንጅል እያለ የሚነግረን ከእርሱ ዘንድ ወርዶ ለዒሣ የተሰጠው ስለ ነቢያችን"ﷺ" መምጣት የሚናገረው ነው፦
3፥3 ተውራትን እና ኢንጂልን አውርዷል፡፡ وَأَنزَلَ التَّوْرَاةَ وَالْإِنجِيلَ
3፥4 ከቁርኣን በፊት ለሰዎች መሪ አድርጎ አወረዳቸው፡፡ "ፉርቃንንም አወረደ"፡፡ مِن قَبْلُ هُدًى لِّلنَّاسِ وَأَنزَلَ الْفُرْقَانَ

"ፉርቃን" فُرْقَان የሚለው ቃል "ፈረቀ" فَرَقَ ማለትም "ለየ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "እውነትን ከሐሰት የሚለይ" ማለት ነው፥ አሏህ ስለ ተውራት እና ኢንጅል መውረድ ከነገረን በኃላ በእነርሱ ላይ የተጨመረውን ሐሰት ከአሏህ ዘንድ ከወረደው እውነት የምንለይበትን ፉርቃን በባሪያው በሙሐመድ"ﷺ" ላይ አውርዷል፦
25፥1 ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስጠንቃቂ ይኾን ዘንድ ያወረደው አምላክ ክብር እና ጥራት ተገባው፡፡ تَبَارَكَ الَّذِي نَزَّلَ الْفُرْقَانَ عَلَىٰ عَبْدِهِ لِيَكُونَ لِلْعَالَمِينَ نَذِيرًا
5፥48 ወደ አንተ መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ እና በእርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በእውነት አወረድን፡፡ وَأَنزَلْنَا إِلَيْكَ الْكِتَابَ بِالْحَقِّ مُصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ مِنَ الْكِتَابِ وَمُهَيْمِنًا عَلَيْهِ

ቁርኣን ከበፊቱ ከአሏህ ዘንድ የወረደውን 4፥136 "ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ" በማለት መለኮታዊ ቅሪትን የሚያረጋግጥ ስለሆነ "ሙሶዲቅ" مُصَدِّق ተብሏል፥ በእርሱ ላይ የጨመሩትን የሚያርም እና የሚቆጣጠር ስለ ሆነ ደግሞ "ሙሀይሚን" مُهَيْمِن ተብሏል። ቁርኣንን ፉርቃን፣ ሙሶዲቅ፣ ሙሀይሚን አርጎ ለሰጠን ለዓለማቱ ጌታ ለአሏህ ክብር እና ምስጋና ይሁን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ


ወሠላሙ ዐለይኩም