Get Mystery Box with random crypto!

#የአከራይ ተከራይ 'ደንቡ' ስግብግብ ተከራዮችን ጭምር ለመቆጣጠር ገደብ ሊበጅለት በተገባ ነበር! | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

#የአከራይ ተከራይ "ደንቡ" ስግብግብ ተከራዮችን ጭምር ለመቆጣጠር ገደብ ሊበጅለት በተገባ ነበር!

ዛሬ ለሥራ ጉዳይ ወደ አንድ ወረዳ ፅ/ቤት ጎራ ብዬ ነበር። ሰሞኑን ለአዲሱ ዓመት በዓል ብሎም ለ6 ወራት ያህል እዚሁ አዲስአበባ ለመክረም ከአሜሪካ የተመለሱ ባልና ሚስት ብሶታቸውን ለሚመለከታቸው እየገለፁ አገኘኋቸው። ንትርኩ ሲጠናቀቅ ቀረብ ብዬ ችግራቸውን ጠየቅኳቸው። ምናልባት የገጠማቸው ችግር የሌሎችም ዲያስፖራዎች ይሆናል በሚል ገፄ ላይ ላካፍላችሁ ወሰንኩ... ነገሩ እንደዚህ ነው፦

ዲያስፖራዎቹ ባልና ሚስት ከሁለት ዓመታት በፊት አዲስአበባ የነበራቸውን ቤት አከራይተው ነበር ወደ አሜሪካ የሄዱት።ለዓመት በዓል ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለሱና በቀጣይነትም ለስድስት ወራት አዲስአበባ ለመቆየት ዕቅድ ስለያዙ ተከራዮቹ ቤታቸውን በመልቀቅ ሌላ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ከአራት ወራት በፊት ከወደ አሜሪካ ደውለው ሲያሳውቋቸው... "አዳነች አቤቤ ቤቱን እንዳትለቁ የሚል ደንብ ስለወጣች ፈፅሞ አንለቅም" በማለት በስልክ ምላሻቸውን ሰጡ። ዲያስፖራዎቹ ምናልባት እኛ በአካል ስንመጣ ይለቃሉ በሚል ግምት በአካል አዲስአበባ ድረስ ቢመጡም ተከራዮቹ "ወይ ፍንክች የአባ ቢላ ልጅ" ሆኑባቸው። እናም አሁን ከውጭ ተመላሾቹ ባልና ሚስት ቤት አልባ ሆነው ከሆቴል ሆቴል እየተንከራተቱ ይገኛሉ። ተከራይ የወጣውን አዋጅ ተገን አድርጎ በሌላ ሰው ንብረት ደረቱን ነፍቶ ለቀጣይ 6 ወራትም እዚያው ለመኖር ወስኗል። ከ6 ወራት በኋላ ደግሞ ደንቡ ዳግም ሊራዘምም ይችላል።

የዲያስፖራዎቹ ቤት ተከራይ በቂ ገቢና ሁለት መኪናዎች ያሉት(ለራሱና ለሚስቱ) እንደሆነ ዲያስፖራዎቹ ነግረውኛል። ኧረ ምን ይኼ ብቻ? ተከራይ የራሱን ቤት ሰርቶ ጨርሶ በውድ ዋጋ አከራይቶ ነው በዲያስፖራዎቹ ቤት ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው የኪራይ ዋጋ ተመን እየኖረ ያለው። ለማንኛውም የወረዳው ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ከፈለጋችሁ ፍርድ ቤት ሂዱና ተከራከሩ ብሎ ሸኝቶአቸዋል። እንግዲህ በተመሳሳይ መልኩ ለዓመት በዓል ከውጭ የሚገቡ ዲያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱት በዓሉን በደስታ ለማክበር ሳይሆን ፍርድ ቤት ለመመላለስ ነው። So sad!

ኑሮ ውድነቱን ሰበብ አድርገው ማህበረሰቡን ሆን ብለው በሚጎዱ አከራዮች ላይ መመሪያው መውጣቱ መልካም ነው። ሆኖም መመሪያውን ተገን አድርገው የራሳቸውን ቤት በውድ ዋጋ አከራይተው በሌላ ሰው ቤት በከረመ የኪራይ ተመን እየኖሩ ዓለማቸውን እየቀጩ ለመኖር በቋመጡት ላይ ግን መቋጫ መበጀት ነበረበት።

መንግስት የዲያስፖራ አባላት ለአዲሱ ዓመት ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ሲያደርግ ይደመጣል፣ ከመጡ በኋላ ግን ቤት እያላቸው በቤታቸው እንዳይኖሩ ግራ-ገብና ገደብ አልባ ደንብ ያወጣባቸዋል። በአሁኑ ወቅት በአከራይና በጋጠ-ወጥ ስግብግብ ተከራይ መካከል ያለውን እንቶ ፋንቶ መታዘብ የፈለገ ወደ ወረዳዎች ሰላምና ፀጥታ ቢሮዎች ብቅ ብሎ ይመልከት። ይሰመርልኝ...የልጥፉ መልዕክት የሚመለከተው የራሳቸውን ቤት ጨርሰው ሰርተው በውድ ዋጋ አከራይተው ተከራይተው የሚኖሩበትን ቤት ለመልቀቅ ፈቃደኛ ያልሆኑ ተከራዮችን ብቻ ነው። መንግስትም እኮ አንድ ሰው የራሱ ቤት ካለው ቀድሞ ተከራይቶ ይኖርበት የነበረውን የመንግስት/የቀበሌ ቤት እንዲለቅ ያስገድዳል። ግለሰቦች ግን በገዛ ንብረታቸው እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ እንዳይወስኑ በ"ደንብ" ስም ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

ስለዚህም የሚመለከታችሁ የአዲስአበባ ኃላፊዎች ደንቡን ወይ አሻሽሉት ካልሆነም አስቀድሞ አዲስአበባ ቤት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት መጥተው በዘገምተኛ የፍርድ ቤት ሂደት እንዳይጉላሉ እዚያው ውጭ ሀገር እያሉ የደንቡ የጊዜ ገደብ እስኪያበቃ ወደ ሀገራቸው እንዳያቀኑ እዚያ እያሉ አሳውቋቸው።

Getahun Heramo