Get Mystery Box with random crypto!

የብልፅግና ፓርላማ ትላንት ከዚህ በኋላ የቤት ኪራይ (ለግዜው የመኖሪያ ቤት) ዋጋ የሚተመነው ጥሮ | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

የብልፅግና ፓርላማ ትላንት ከዚህ በኋላ የቤት ኪራይ (ለግዜው የመኖሪያ ቤት) ዋጋ የሚተመነው ጥሮ ግሮ ባገኘው ገንዘብ ቤቱን በሰራው ሰውዬ ሳይሆን፣ ቤቱ ሲሰራ ድንቡሎ ያላዋጣ፣ ቢሮ ቁጭ ያለ የሆነ ባለስልጣን (መንግስት) ነው የሚል አዋጅ አፅድቋል።

በነገራችን ላይ የንብረት ባለቤትነት መብት የመብቶች ሁሉ ቁንጮ ነው፣ የሰው ልጅ በህይወት መኖር የሚችለው ደክሞ ያፈራውን ሀብት በነፃነት መጠቀም ሲችል ነው። ስለዚህ የንብረት መብትህ ተጣሰ ማለት በህይወት የመኖር መብትህ ተጣሰ ማለት ነው። ካልተሳሳትኩ አዋጁ በህገ መንግስቱ ከተቀመጠው የንብረት መብት ጋር ሁሉ ይጣረሳል።ይሄን ለህግ ሰዎች ትተን እኛ ወደ ኢኮኖሚክሳችን እንሂድ።

መቼም ፈርዶብኝ ኤንጂ ስለ ዋጋ ተመንና ውጤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማብራራት አይጠበቅብኝም ነበር። ምክንያቱም ውጤቱን በሲሚንቶ፣ በዘይት፣ በስኳር ወዘተ በአይኑ በብረቱ አይቶታልና። (ተመሳሳይ ነገር እየሰራ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ሰው ነሆለል ነው ያለው ማን ነበር?)

ሲጀመር የቤት ኪራይ ያሳየው ጭማሪ ከሌላው ሸቀጥና አገልግሎት የተለየ አይደለም፣ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ኩንታል ጤፍ ስድስት ሺ ብር ሲሸጥ፣ እኔ ያለሁበት አከባቢ የባለ ሁለት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ዋጋ ዘጠኝ ሺ ብር ገደማ ነበር። አሁን ጤፉ አስራ ሶስት ሺ ብር ሲሆን ቤቱ ደግሞ ሀያ ሺ ብር ገብቷል። ቤቱን በዘጠኝ ሺ ብር አከራይቶ ጤፍ ሸምቶ በተረፈው ሌላ ሸቀጥ ይገዛ የነበረ ሰው አሁንም በሀያ ሺ ብሩ መሸመት የሚችለው ተመሳሳይ ነገር ነው። የጨመረው ሲሸጥ ይቀበልና ሲገዛ ይሰጥ የነበረው የገንዘብ መጠን ብቻ ነው፣ ያገኘው አዲስ የመግዛት አቅም የለም። ከእያንዳንዱ ልውውጥ ውስጥ በዚህ መልኩ ብሩን እያወጣን እቃን በእቃ እየመዘንን ብናየው ውጤቱ ተመሳሳይ ነው።

የጨመረው የእቃው ዋጋ ሳይሆን የልውውጥ አማካኙ (የወረቀት ብሩ) መጠን ነው፣ ይሄ ማለት ችግሩን እየፈጠረ ያለው ባለ ብሩ ነው ማለት ነው። የሆነ አካል ባዶ ወረቀት ይዞ ገበያ እየመጣ እሴት ባለው ነገር ለውጦ ወደቤቱ ይሄዳል ማለት ነው።ብር የማተም ብቸኛ ስልጣን ያለው ማን እንደሆነ ደግሞ ይታወቃል። በሚገርም ሁኔታ ችግሩን የፈጠረው አካል ችግሩን የፈጠራችሁት እናንተ ናችሁ፣ እናንተ ለፈጠራችሁት ችግር መፍትሄ አመንጪ ደግሞ እኔ ነኝ ባይ ነው።

በነገራችን ላይ በዚህ አዋጅ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ ተከራይ ነው( ገፈት ግን ምንድነው ጎበዝ)። ምናልባት ለተወሰነ ግዜ በአዋጁ ኢንጆይ ያደርግ ይሆናል።መጪው ግዜ ግን ለእርሱ ድቅድቅ ጨለማ ነው። ምክንያቱም ሰው በገዛ ገንዘቡ በሰራው ነገር ላይ አዛዥ፣ ባለቤትና ተጠቃሚ የማይሆን ከሆነ የግዜ ጉዳይ ነው እንጂ ብሩን(ካፒታሉን) ሌላ መንግስት ወደማይቆጣጠረው ስራ ያዛውረዋል።ስለዚህ ከጥቂት ግዜ በኋላ የቤት አቅርቦት ይቀንሳል፣ አቅርቦት ይቀንሳል ማለት ደግሞ ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው።የአቅርቦትና ፍላጎትን ህግ ተከትሎ የሚፈጠረውን ዋጋ ደግሞ በአዋጅ አታቆመው፣ በፓሊስ አታቆመው፣ በታንክ አታቆመው፣ በድሮን አታቆመው።

የቤት ኪራይን ችግር መንግስት የምር መቅረፍ ከፈለገ ማድረግ የሚገባው ሁለት ነገር ነው። አንደኛ በየግዜው ዋጋ እየጨመረ ያለው በግሽበት ምክንያት ስለሆነ ኪራይ እንዳይጨምር ግሽበቱን ማቆም። ሁለተኛ የቤት እጥረት የተከሰተው መሬቱ በመንግስት ተቀፍድዶ በመያዙ ስለሆነ አቅርቱቦት እንዲጨምር መሬቱን የግል ማድረግ ነው። ከዛ ውጭ ያለው ሙከራ ከንቱ ድካም ነው።

Mekoya Kebede