Get Mystery Box with random crypto!

“ሕዝቡ የፓርክ ሳር እና አበቦች የሚያገኙትን ያህል ውሃ እንኳን እያገኘ አይደለም”- የአዲስ አበባ | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

“ሕዝቡ የፓርክ ሳር እና አበቦች የሚያገኙትን ያህል ውሃ እንኳን እያገኘ አይደለም”- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የውሃ አቅርቦት ችግር እንዳለ የከተማዋ ነዋሪች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ተናግረዋል። 

“መንግስት መጀመሪያ የሕዝቡን የውሃ አቅርቦት ችግር ሳይፈታ የመንገድ ላይ እና የፓርኮችን አትክልቶች በቀን ሶስት ጊዜ ሲያጠጡ መዋል አግባብነት የሌለው ነው” ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ የሆነ የውሃ አቅርቦት ችግር እንዳለ እና ችግሩን ለማስተካከል እየተሰራ ያለ የሚታይ ጥረት አለመኖሩን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተረድታለች። 

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 4፣5 እና 7 አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃ ችግር እንዳለ እና በሳምንት አንድ ጊዜ የሚመጣው ውሃ በበቂ ሁኔታ ሳይዳረስ እና የሚመጣበትም ሰአት ለሊት በመሆኑ ለመቅዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የነዋሪዎቹን ቅሬታ በመያዝ አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣንን ለማነጋገር ባደረገችው ጥረት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ነገር ግን በተለያዩ አካባቢዎች ውሃ በሳምንት አንድ ቀን እንደሚመጣና ኃይል የሌለው በመሆኑ አንድ ጀሪካን ለመሙላት ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ይፈጃል ሲሉ ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ። 

“እሱን ሌሊት ስንቀዳ አድረን ጠዋት ተነስተን ስራ መግባት አልቻልንም። ከሳምንት ሳምንት መድረስም ከብዶናል” ሲሉም ጠቁመዋል። 

በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ የአካባቢው ሰው ገንዘብ በማዋጣት የታንከር ውሃ በመኪና እያስመጡ እየተጠቀሙ እንደሆነ እና ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን እንዲሁም በመኪናው ለሚመጣው ውሃ የመክፈል አቅም የሌላቸው ሰዎች በእጅጉ እየተጎዱ መሆኑን ቅሬታቸውን አመላክተዋል። 

እንዲሁም በልደታ ክፍለ ከተማ ልደታ መናፈሻ አካባቢ “ውሃ ከጠፋ አንድ ወር ሆኖታል” የሚሉት ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ እየገዙ እንደሚጠቀሙ፤ ነገር ግን ልብስም ሆነ እቃዎችን ለማጽዳት እየተቸገሩ መሆኑን ለአዲስ ማላዳ ተናግረዋል። 

በተመሳሳይ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቤተል ሮም ሰፈር ባጃጅ መጨረሻ “ንጹህ ውሃ ካየን አመት አለፈን በሳምንት ሁለት ቀን የሚለቀቅልን በጣም የቆሸሸ እና የተበከለ ነው። በመሆኑም ንጹህን ውሃ በሮቶ እያመጡ ይሸጣሉ ይህ ደግሞ ወንጀል ነው” ሲሉ ያሉበትን ችግር አስረድተዋል።