Get Mystery Box with random crypto!

መጋቢት ፲፫ ፩፰፻፺፰ ዓ.ም ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ያረፉት ቀን ነበር። የገናናው የሸዋ | ታሪካዊት ኢትዮጵያ [ Historical Ethiopia ]

መጋቢት ፲፫ ፩፰፻፺፰ ዓ.ም ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ያረፉት ቀን ነበር።

የገናናው የሸዋ ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ የልጅ ልጅ፣ የታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የአክስት ልጅ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት የሆኑት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ያረፉት መጋቢት ፲፫ ቀን ፩፰፻፺፰ ዓ.ም ነበር።

ስመ ጥሩ የሸዋ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ ልዕልት ተናኘወርቅን ወለዱ፤ ልዕልት ተናኘወርቅ ደግሞ ወልደሚካኤል ወልደመለኮት አግብተው ልዑል ራስ መኮንንን ወለዱ፡፡ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት ግንቦት ፩ ቀን ፩፰፶፬ ዓ.ም ጎላ ወረዳ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ነው፡፡ ገና በወጣትነታቸው ወደ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ሄደው ከአጎታቸው ልጅ ከንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ጋር ተዋውቀው ቤተሰባዊና ዝምድናቸውን አጸኑ፡፡

በፀባያቸውም ታገሽና አስተዋይ ስለነበሩ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ወዳጆች በመሆን እንደ አባትና ልጅ ይተያዩ ጀመር፡፡ የሐረርጌን ግዛት በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ ሆኑ፡፡ ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ተነስተው በዘመኑ ከንጉሥ በመቀጠል ከፍተኛ ለሆነው የ‹‹ራስ›› ማዕረግም በቁ፡፡ልዑል ራስ መኮንን የአጼ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ሀገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለአጼ ምኒልክም አሳውቀዋል።

የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሰራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ እስከ አድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ልዑል ራስ መኮንን ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ ሊያደርጓቸው ያስቡ ነበር፡፡
ነገር ግን እምዬ ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ልዑል ራስ መኮንን መጋቢት ፲፫ ቀን ፩፰፻፺፰ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ሞታቸው በንጉሰ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት (አዲስ አበባ) በተሰማ ጊዜም ከፍተኛ ሀዘን ሆነ፡፡ ታላቁ ንጉሥ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም አምርረው አለቀሱ፡፡ በወቅቱም ይህንን የተመለከቱ ሰዎች እንዲህ ብለው ገጠሙ …

‹‹ዋ አጤ ምኒልክ እግዚአብሔር ያጥናዎ፣
በየበሩ ቋሚ ከላካይ ሞተብዎ፡፡
ሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ፣
ምን ዋስ አገኘና ሐረርጌ ተፈታ፡፡
ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሳሳና በራ ገለጣቸው፣
እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው፡፡››
ከአልቃሾቹ መካከል አንደኛው ደግሞ የልዑል ራስ መኮንንን ደግነት ለማስታወስ እንዲህ ብሎ ሙሾ አወረደ …
«ስልከኛው ሲያረዳ ነገር ተሳሳተው፣
መኮንን አይደለም ድሀ ነው የሞተው፡፡»




ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ !!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!

YOUTUBE : https://youtube.com/@Historical_Ethiopia
ጥያቄ ካለዎት @Historical_Ethiopia_Discussion
የቴሌግራም ቻናል - @Historical_Ethiopia