Get Mystery Box with random crypto!

ደስታዬን ተምኑልኝ በ 48 ሰአት ውስጥ ሁለት አስቸጋሪ የሚባል የልብ ቀዶ ጥገና ሰርቼ ስለነበር | Healing Valves Ethiopia

ደስታዬን ተምኑልኝ

በ 48 ሰአት ውስጥ ሁለት አስቸጋሪ የሚባል የልብ ቀዶ ጥገና ሰርቼ ስለነበር በድካም የዛለውን አካሌን ላሳርፍ ስል በቴሌግራም አማካኝነት ከቱርክ ኢስታንቡል በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ መልእክት አይኔን በእንባ; ልቤን በሀሴት ልፋቴን በድል ሞላው::
ከሁለት አመት ተኩል በፊት በቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒቲል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማካሄድ ወረፋ ደርሶት በሆስፒትል ቢገኝም በቅድመ ዝግጅት ምርመራ በሁለት የልብ በሮች ላይ ከፍተኛ የሚባል ችግር እንዳለ ተነግሮት በቅድሚያ ይህ ከፍተኛ የህይወት አድን የልብ ቀዶ ጥገና አካሂደህ ከተረፍክ ብቻ ተመለስ ስለተባለ ወጣት አጫውቼአቹህ ነበር:: ከስምንት ወር በፊትም በወጣው የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ መፅሀፌም ላይ " ላያስችል አይሰጥ" በሚል ንኡስ አርእስት የቀረበው የዚህ ወጣት ታሪክ ሲሆን በሀኪም ፔጅም ላይ የዚህ የልብ ቀዶ ጥገና ስኬት አቅርበን ነበር:: ህይወቱን በዳያሊስስ (dialysis) ላይ ያደረገውና አይሳካለትም የተባለው ወጣት ሁለት የልብ በር ቅየራ የልብ ቀዶ ጥገና (Double Valve replacement surgery for patient on dialysis in our country by the local team)በድል አጠናቀቀ:: ይሁን እንጂ በሀገራችን ይሰጥ የነበረው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተቋረጠ:: በCOVID-19 ወረርሽኝ መከሰት እና መያዝ ሲቀጥልም በሌሎች ቤተሰባዊ ችግር ይህ ታካሚ ተስፋ ቆርጦ በዳያሊስስ (dialysis) ላይ እንዳለ ከሁለት አመት በላይ የተቀመጠ ሲሆን የኛም የልብ ቀዶ ጥገና ህይወቱን ቢያተርፈውም ለታሰበለት አላማ ባለመዋሉ እዝነን ነበር::
እነሆ ይህንን ታሪካዊ የልብ ቀዶ ጥገና በሰራን ከሁለት አመት ተኩል በህዋላ ዛሬ ማታ የተንቀሳቃሽ ምስል ድጋፍ ያለው መልእክት እንዲህ ይላል" በቱርክ ኢታንቡል የኩላሊት ንቅለ ተከላው በሰላም ትካሂዶልኝ በመልካም ሁኔት እያገገምኩ እገኞለሁ ምስጋናዬም ለአንተና ለመላው የልብ ህክምና ቡድን ይድረሳቹህ " ሲል እንባ የተናነቀው ያ የማውቀው እና የማይሰበረውን ወጣት በደስታ ሰክሮ አየሁት:: እኔም የነዘነዝኳቹ በምክንያት ነበረና ደስታዬን መዝኑልኝ ደስታዬንም ተካፈሉኝ አልኳቹህ::