Get Mystery Box with random crypto!

‹‹ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል›› (መዝ. ፹፰፥፲፪) በትንቢት ‹‹ታቦርና አርሞንኤም | የኖህ መርከብ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ

‹‹ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል›› (መዝ. ፹፰፥፲፪)

በትንቢት ‹‹ታቦርና አርሞንኤም በስም ደስ ይላቸዋል›› ብሎ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ (መዝ. ፹፰፥፲፪)

በዚህችም ቀን መድኃኒታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡

ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደእርሱ መጡ፡፡ ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው፤ ‹‹አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን? ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።››

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሳበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና።

እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችን ጌትነቱን የሚገለጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱንም ስሙት። ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ። ስለ እርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነብያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።
ምንጭ:መጽሐፈ ስንክሳር
እንኳን አደረሳችሁ!