Get Mystery Box with random crypto!

#ሐምሌ_5 #ቅዱስ_ጳውሎስና_ቅዱስ_ጴጥሮስ ሐምሌ አምስት በዚች ቀን የክቡራንና የዐበይት አባቶቻች | የኖህ መርከብ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ

#ሐምሌ_5
#ቅዱስ_ጳውሎስና_ቅዱስ_ጴጥሮስ

ሐምሌ አምስት በዚች ቀን የክቡራንና የዐበይት አባቶቻችን ሐዋርያት #የቅዱስ_ጴጥሮስ እና #የቅዱስ_ጳውሎስ የሰማዕትነታቸው መታሰቢያ ነው።

በዚህች ዕለት ስለክርስቶስ የተገፋ፣ ስለክርስቶስ የተወገረ፣ ስለክርስቶስ የተሰደደ፣ ስለክርስቶስ የታሰረ፣ ስለክርስቶስ ከአለም ሃሳብና መሻቷ የተለየ፣ ስለክርስቶስ ራሱን የለየ፣ ስለክርስቶስ ምእመናን ያነፀ፣ ስለክርስቶስ መልካምን መልእክት የፃፈ #ቅዱስ_ጳውሎስ ሰማዕት ሆነ። ነገር ግን በስጋ ሞተ በመንፈስ ግን ህያው ነው፤ የፅድቅን አክሊል ተቀበለ ከክርስቶስ ጋር መኖርን እንደናፈቀ አገኛት፤ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳን ማህበር ተቀላቀለ ከመላእክት ምስጋና ተጋራ በስጋ ህይወቱ ከእውቀት ከፍሎ እንዳወቀ በሰማያዊው ኑሮ በእጅጉ የበለጠ እውቀትን ተቸረ። በማይጠወልግ፣ በማይደርቅ፣ በማይዝል፣ ፍሬያማም በሆነ ክርስቶስ ግንድነት ላይ ቅርንጫፍ ሆኖ ተሰርቷልና በስጋ ኑሮው በድካም ዝለት ጠውልጎ እንደነበረ የሚጠወልግ አይደለም፤ በማስተማር ብዛት ጉሮሮው እንደደረቀ አሁን የሚደርቅ አይደለም፤ በብርቱ ክንድ ላይ በምቾት አለና የሚዝልም አይደለም፤ ክፉወች ሮማውያን ግን ቅዱስ ጳውሎስን ገደልን አሉ። አይሁድም እፎይ ጳውሎስ ሞተ አሉ። ቅዱስ ጳውሎስ ግን የናፈቀው ክርስቶስ ጋር ሊኖር ወደ ዘለዓለማዊው ህይወት ሄደ፤ ራሱን ህያው መስዋእት አድርጎ በክርስቶስ ፊት እንደ ንፁህ መገበሪያ ስንዴ ተፈጨ፤ አይሁድ በጳውሎስ መሞት ድል ያደረጉ ይመስላቸዋል ነገር ግን የፅድቅን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ ከፀሃይ ይልቅ እያበራ በሰማይ ሆኖ ቅዱስ ጳውሎስ አለ በማይደርቅ ግንድ ላይ የተተከለ ቅዱስ ጳውሎስ ፍሬ በሙላት የያዘ የለመለመ ቅርንጫፍ ሆኖ አለ በቅድስና በተዋበ የክርስቶስ አካል መካከል መልካም ብልት ሆኖ አለ፡፡

አይሁድ ግን ቅዱስ ጳውሎስን ገደልን አሉ በሰይፍ አንገቱን ቆርጠው በስጋ ገድለውታልና አላዋቂ አይሁድ ከሮማውያን ጋር አብረው ጳውሎስን ገደልን አሉ፤ እርሱ ግን ከአፈር በተበጀ ስጋ ሞት ቢሞት በእግዚአብሔር እስትንፋስ ስለተሰጠች ነፍስ ህያው ነው፡፡

ዳግመኛም በብርሃኑ ብርሃንን በጨውነቱ መጣፈጥን በመድሃኒቱ መፈወስን የሰጣቸው ተወዳጅ የሐዋርያት አለቃ #ቅዱስ_ጴጥሮስን አይሁድ ቁልቁል ሊሰቅሉት ወደ ሮም አደባባይ ከወዳጁ ከጳውሎስ ጋር አጣደፉት፤ ጴጥሮስ ግን በትምህርቱ ብርሃን ጨለማቸውን ገፍፎላቸው፣ በእምነት መድሃኒት ሙታናቸውን አንስቶላቸው፣ ጎባጣቸውን አንቅቶላቸው አንካሳወቻቸውን አፅንቶላቸው ክፉ ጠላት ዲያብሎስንም አባርሮላቸው ነበር አይሁድ ግን ከወዳጃቸው ጴጥሮስ ይልቅ ጠላቶቻቸውን ሮማውያን ጋር አብረው አንድም ከወዳጃቸው ከክርስቶስ ይልቅ ከጠላታቸው ዲያቢሎስ ጋር አብረው ቅዱስ ጴጥሮስን እንደጌታውና መምህሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሊሰቅሉት ወደሮም አደባባይ አፋጠኑት። የማይጠፋውን ፋና ሊያጠፉ የማይደበዝዘውን ብርሃን ሊያደበዝዙ የማይሞት የክርስቶስን ልጅ ሊገድሉ በገሃነም ደጆች የማትናወጥ ክርስትናን ሊያናውጡ አይሁዳውያን የክርስቲያኖች ዋና ያሉትን ቅዱስ ጴጥሮስን በብዙ ስቃይ አንገላቱት፤ ተወዳጅ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን የስጋ ሞቱ ዕረፍቱ እንደሆነ እጅግ አስቀድሞ አውቆ ነበር የአይሁድ ማሰቃየት ወደ ክርስቶስ የፀጋ ግምጃ ቤት እንደሚያደርሰው አውቆ ነበር የአይሁድ መጨከን ወደ ክርስቶስ አማናዊ ፍቅር እንደሚመራው አውቆ ነበር፤ “ገደልንህ” አሉት። እርሱ ግን “ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት ክርስቶስ ገፋችሁኝ” አላቸው። “ክርስቲያኖችን ጨረስን” አሉት እርሱ ግን “የእኛ ሞት የክርስቲያኖች ዘር ነው” አላቸው፤ “አንተ ርጉም” አሉት እርሱ ግን “የክርስቶስ ምህረት በእናንተ ላይ ይሁን” ሲል በፍቅር ፀለየላቸው፡፡

እነሆ አባቶቻችን እነሆ ዋኖቻችን በክፋት በአንዳች እንኳን የሚከሰሱበት ምክንያት አልተገኘም በቀማኝነትም ማንም እነሱን ሊከስ የሚችል የለም ነገር ግን የሚሰድቧቸውን መረቁ ለሚያሳድዷቸው ፀለዩ ለተራቡት ምግብን ለተጠሙት መጠጥን አቀበሉ ድሆችን ተንከባከቡ ድውዮችን ፈወሱ የጨለማን ክፋት በፍቅር ብርሃን አረከሱ የዲያብሎስን ጭካኔ በክርስቶስ ርህራሄ ሰበሩ፡፡ እነሆ አባቶቻችን አስቀድመው ክርስቶስን አይተው ነበርና ክርስቶስን በትምህርቱ በተአምራቱ በሞቱም መሰሉት፡፡

እንኳን ለቅዱስ ጴጥሮስና ለቅዱስ ጳውሎስ አመታዊ መታሰቢያ እለት አደረሰን፡፡ በረከታቸው ይደርብን። አሜን!!