Get Mystery Box with random crypto!

#ልብ_ብለው_ያንብቡ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘእንዚናዙ ለንስሓ ልጁ በሰርጓ ቀን መገኘት ባለመቻሉ የላ | ✞ትንሽ ዝምታ ✞

#ልብ_ብለው_ያንብቡ

#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘእንዚናዙ ለንስሓ ልጁ በሰርጓ ቀን መገኘት ባለመቻሉ የላከላት ደብዳቤ

“ልጄ! ለሰርግሽ የነፍስ አባትሽ እኔ ጐርጐርዮስ ይህን ግጥም ስጦታ አድርጌ ልኬልሻለሁ፡፡ አባት ለሚወዳት ልጁ ሊሰጣት የሚችለው የተሻለው ምክርም ይህ እንደ ኾነ አምናለሁ፡፡

“ኦሎምፒያታ ሆይ፥ እውነተኛ ክርስቲያን ለመኾን ያለሽን ፍላጎት ዐውቃለሁና በደንብ አድምጪኝ! እውነተኛ ክርስቲያን እንዲሁ መኾንን የሚመኝ ብቻ ሳይኾን እንደዚያ ለመኾን ሊጥር ይገባዋል፡፡

“ከኹሉም በላይ፥ እግዚአብሔርን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ከእርሱ ቀጥሎም በቅዱስ ወንጌል እንደ ታዘዘው እንደ ጌታችንና መድኃኒታችን [ኢየሱስ ክርስቶስ] አድርገሽ ባልሽን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ስለዚህ እጠይቅሻለሁ! ጌታዋንና ፈጣሪዋን [ኢየሱስ ክርስቶስን] የማታከብርና የማትወድ ሴት በዚህ መንገድ ባልዋን እንዴት አድርጋ ልታከብረውና ልትወደው ትችላለች?

“በጋብቻሽ ውስጥ የትዳር አጋርሽ ይኾን ዘንድ እግዚአብሔር መርጦ ለሰጠሽ ባል ያለሽ መውደድ፣ ስሜትና ፍቅር እጅግ ኃያል ሊኾን ይገባዋል፡፡ ይህ ሰው አሁን የሕይወትሽ ዓይን፣ የልብሽም ደስታ ነውና፡፡

“እግዚአብሔርን እንደምትወጂው፥ ባልሽንም ያለ ቅድመ ኹኔታ ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ አንቺ ሴት እንደ ኾንሽና ታላቅ የኾነ ዓላማና ግብ እንዳለሽ፥ ኾኖም ዓላማሽና ግብሽ የቤትሽ ራስ ሊኾን ከሚገባው ባልሽ የተለየ እንደ ኾነ ዕወቂ፤ ተረጂም፡፡ ባንቺ ዕድሜ ላይ ያሉት አንዳንዶች ኹለቱም ፆታዎች እኩል [ራስ ናቸው] ብለው የሚሰብኩትን አትስሚ፤ የጋብቻንም ግዴታ [ወይም ዋና ዓላማ] አስቢ፡፡ እነዚህን ግዴታዎች [ወይም ዓላማዎች] ስታውቂ የቤተሰብሽን ተግባራት ለማከናወን እንደ ምን ያለ ትዕግሥትና ጽናት እንደሚያስፈልግሽ ታውቂያለሽና፡፡ እንደ ሚስት እጅግ ጥንካሬን ገንዘብ የምታደርጊውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

“ወንዶች እንዴት በቀላሉ የሚቈጡ መኾናቸውን በርግጥ ልታውቂ ይገባሻል፡፡ አይችሉም፤ ብዙ ጊዜም እንደ በረኻ አንበሳ ይኾናሉ፡፡ እንግዲህ ሚስት ጸንታ ልትቆምና የነፍስ ልዕልናዋን ልታሳይ የሚገባት በዚህች ቅጽበት ነው፡፡ አንበሳን የማስለመድ ሥራ መሥራት አለብሽ፡፡ አንበሳን የሚያስለምድ ሰው አንበሳ ሲያገሳ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝም ጸጥ ይላል፡፡ በጸጥታውና በርጋታውም የአንበሳውን ቊጣ ይቈጣጠራል፡፡ በርጋታና በለሆሳስ ኾኖ ያናግረዋል፤ ይደባብሰዋል፤ በቀስታ ያሻሸዋል፤ በጥቂት በጥቂቱም አንበሳው ቊጣውን ይተዋል፡፡

“ባልሽ ስሕተት ሲሠራ በፍጹም ልትነቅፊው፣ ልትንቂው ወይም ልታስነውሪው አይገባም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንድ መሥራት ያለበትን ነገር ባይሠራና ከዚሁ የተነሣም ውጤቱ ደስ የማያሰኝ ቢኾን፣ ወይም እጅግ የምትፈልጊውና አግባብ ነው ብለሽ የምታስቢውን ባያደርግ እንኳን ባልሽን መናቅ ከአንቺ ልታርቂ ይገባል፡፡ ክፉዎች አጋንንት ዘወትር ቤታችሁን ለማፍረስና የጥንዶች መንፈሳዊ አንድነትን ለመበተን እንደሚሞክሩ ዕወቂ፡፡”

( #ከገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ከትንሿ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ የተወሰደ)