Get Mystery Box with random crypto!

ዕንባዊ መሰረት '''''''' ''''''''' እንደ እሳት ተቀምጠሽ በውበት ነበልባል ሆነሽ ከበላዬ | አብርሃም ፍቅሬ (የቅዳስ ልጅ)

ዕንባዊ መሰረት
"""""""" """""""""
እንደ እሳት ተቀምጠሽ
በውበት ነበልባል ሆነሽ ከበላዬ፤
በመፋጀትሽ ልክ
እንባዬን ባነባ
"የወንድ ንፍርቅ" ብለሽ ተሳለቅሽ በእንባዬ!

(አይ አንቺ)

እሳት አንቺነትሽ
በሻማ እኔነቴ ከበላዬ ሲውል፤
አዘቅዝቄ ሳለቅስ
አልገባሽም ከቶ የመነፍረቄ ውል!

(አየሽ)

ሻማ ያነባውን
ላለመንገዳገድ
ከመቅረዙ አፍሶ ረግጦ ነው የቀና፤
የኔንም ተመልከች
በእንባ መሰረት
ስብርብር ጉልበቴ ጠንክሮ ሲፀና...

(አየሽ)

የሰው ልጅ ሲያለቅስ
አቅመ ቢስ
ልፍስፍስ
አስመስሎ በሰው ማየት ቢያስለምድም፤
በሀዘኑ ፀንቶ
በእንባው የቆመ ሰው
ከጊዜ በኃላ አይንገዳገድም..!

አብርሃም ፍቅሬ
(የቅዳስ ልጅ)

@HAKiKA1
@HAKiKA1