Get Mystery Box with random crypto!

ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው? ጳውሎስ ይህን መልእክት ለማን እንደላከ ሲገልጽ፥ «በኃይማ | Grace Channel™

ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

ጳውሎስ ይህን መልእክት ለማን እንደላከ ሲገልጽ፥ «በኃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ» ይላል። ቲቶ በሁላት ልዩ መንገዶች የጳውሎስ ልጅ ነበር። በመጀመሪያ፥ ቲቶ የጳውሎስ መንፈሳዊ ልጅ ነበር። ምናልባትም ቲቶ በክርስቶስ እንዲያምን በመሣሪያነት ያገለገለው ጳውሎስ ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛ፥ ቲቶ ከጳውሎስ፥ የቅርብ ጓደኞችና የጉዞ ባልደረቦች አንዱ በመሆኑ የጳውሎስ ልጅ ነበር።
ስለ ቲቶ ብዙ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ማንነቱ፥ የመጣበት አካባቢ፥ ወዘተ… በዝርዝር ሰፍሮ አንመለከትም። ምንም እንኳ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ ባይገኝም፥ የጳውሎስ መልእክቶች እንደሚያሳዩት ቲቶ ከጳውሎስ የቅርብ ባልደረቦችና የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞዎቹ አጋዦች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። በመጀመሪያ ስለ ቲቶ የምናነበው ከገላትያ መልእክት ውስጥ ነው። በገላትያ መልእክት ውስጥ ቲቶ አሕዛብ ሲሆን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መገረዝ የሚያስፈልገው መልካም የአሕዛብ አማኝ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል። ይህ ከፊል አሕዛብና ከፊል አይሁዳዊ ሆኖ ሳለ ጳውሎስ ከገረዘው የጢሞቴዎስ ሁኔታ የተለየ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ቲቶ ከገላትያ ወይም ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መምጣቱን አይናገርም። በተጨማሪም ከመጀመሪያው የጳውሎስና የበርናባስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ሰኋላ ማመን አለማመኑ አልተጠቀሰም።
የአሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ አለባቸው ወይም የለባቸውም የሚለው ክርክር በተጧጧፈበት ወቅት ጳውሎስና በርናባስ ቲቶን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። ቲቶ የተመረጠው ምናልባትም ጥልቅ መንፈሳዊነት የነበረው ሰው በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስና በርናባስ አሕዛብ ክርስቲያን መገረዝ ሳያስፈልገው በመንፈስ ቅዱስ ሊሞላና የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ ሊመላለስ እንደሚችል ለአይሁድ ክርስቲያኖች ለማሳየት ፈልገው ነበር። የቲቶን መንፈሳዊነት መመልከታቸው የአይሁድ መሪዎች የአሕዛብ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት መገረዝ አለባቸው በሚለው ክርክር ላይ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲይዙ ሳይረዳቸው አልቀረም። የአይሁድ መሪዎች ቲቶ ባይገረዝም እንደ ክርስቲያን ሊቀበሉት ችለዋል።
ቲቶ ከጳውሎስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞዎች ውስጥ በምን ያህሎቹ ላይ አብሮ እንደተጓዘ አልተጠቀሰም። ነገር ግን ከጳውሎስ ጋር ለረጅም ጊዜ በማገልገሉ ምክንያት ለትላልቅ አገልግሎቶች እንደ ተሾመ እንመለከታለን። በጳውሎስ ሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ላይ፥ ቲቶ ከጳውሎስ ጋር በኤፌሶን ነበር። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን ከጻፈ በኋላ በእርሱና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ቲቶ መልካም የአስተዳዳሪነት ስጦታ የነበረውና እንደ ጢሞቴዎስ መጋፈጥን የሚፈራ ሰው አልነበረም። በመሆኑም ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የነበሩትን ችግሮች በማስተካከል ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ገንዘብ የማሰባሰቡን ተግባር እንዲጀምሩ ያበረታታቸው ዘንድ ቲቶን ወደ ቆሮንቶስ ላከው። ምናልባትም የጠፋውንና 2ኛው የቆሮንቶስ መልእክት በመባል የሚታወቀውን ለክርስቲያኖች የወሰደው ቲቶ ሳይሆን አይቀርም። ቲቶ በቆሮንቶስ የነበረውን ሁኔታ በዘዴ ለማስተካከል ችሏል። ቲቶ በመቄዶኒያ ከጳውሎስ ጋር በተገናኘ ጊዜ፥ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ የነበራቸውን አመለካከት ቀይረው ነበር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን ጽፎ በቲቶ በኩል ወደ ቆሮንቶስ ላከ። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ፍቅር የነበረው ቲቶ ክርስቲያኖች የጳውሎስን መመሪያዎች በመከተል ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ገንዘብ የማሰባሰቡን ተግባር እንዲጀምሩ ሊረዳቸው ችሏል። ጳውሎስ ቲቶን እንደ ባልደረባውና የወንጌል አገልግሎት ተባባሪ አድርጎ ይቆጥረውና ያከብረው ነበር።
ጳውሎስ ታስሮ በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ቲቶ ስለደረሰበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚለው የለውም። ጳውሎስ ከተፈታ በኋላ ቲቶ ከጳውሎስ ጋር በመተባበር አራተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው የሚባለውን አገልግሎት ያከናወነ ይመስላል። ጳውሎስና ቲቶ ወደ ቀርጤስ ከተማ ሲደርሱ፥ ጳውሎስ ቲቶ በዚያ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያደራጅ አደረገ። ከዚያ ጳውሎስ ወደ ኤፌሶንና መቄዶኒያ ተጓዘ። በዚህም ጊዜ ቲቶ የሚደርስበትን ተቃውሞ ለማሸነፍ ሥልጣኑን እንዲጠቀምና እውነትን እንዲያስተምር አሳስቧታል። በኋላ ግን ሌሎች መሪዎች በቲቶ እግር በመተካታቸው በኒቃፖሊስ ከጳውሎስ ጋር ሊገናኝ ችሏል። ኒቃፖሊስ ከግሪክ በምዕራባዊ ዳርቻ የምትገኝ ከተማ ነበረች። በኋላ በደልማጢያ (ያሁኗ ዩጎዝላቪያ) እንዲያገለግል የተጠየቀ ይመስላል። ጳውሎስ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ሁለተኛውን የጢሞቴዎስ መልእክት በጻፈበት ወቅት ቲቶ በዚያች ከተማ ውስጥ ያገለግል ነበር። አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚለው፥ ከዚያ በኋላ ቲቶ ወደ ቀርጤስ ተመልሶ ጳጳስ ሆኗል። በዚህም በደሴቲቱ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት የማስተባበሩን ተግባር አከናውኗል።
የቀርጤስ ደሴት የምትገኘው ከግሪክ በስተደቡብ ነበር። ይህቺ ደሴት 350 ኪ.ሜትሮች ያህል ርዝመት ያላት ሰፊ ስፍራ ነበረች። ቤተ ክርስቲያን በዚህች ደሴት ውስጥ እንዴት እንደ ተመሠረተች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የገለጸው ነገር የለም። በበዐለ ኀምሳ በክርስቶስ ያመኑ አንዳንድ የቀርጤስ ሰዎች እንደነበሩ ይናገራል (የሐዋ. 2፡11)። ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም በሚሄድበት ጊዜ የቀርጤስን ደሴት ጎብኝቷታል። በዚህ ጊዜ በዚህች ከተማ ውስጥ የስብከት አገልግሎት ለመስጠት የተፈቀደለት መሆኑ አልተገለጸም። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ፈቃድ ያገኘ አይመስልም። ጳውሎስ ከመጀመሪያው የሮም እሥራት ከተፈታ በኋላ፥ ወደ ቀርጤስ ተመልሶ እገልግሏል። ሌሎችን አካባቢዎች ለመጎብኘት በፈለገ ጊዜ፥ ቲቶ በዚያ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያደራጅ አድርጓል። ስለሆነም ጳውሎስና ቲቶ ይህችን ቤተ ክርስቲያን በጋራ የመሠረታት ይመስላል። ቲቶ አመራሩን የማደራጀቱን ተግባር ለብቻው ተወጥቷል። ምናልባትም ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲስና ብዙ ምእመናን ያልነበሯት በመሆኑ ይመስላል ዲያቆናትን መሾም አላስፈለገም።
የቀርጤስ ሰዎች ወደ ደሴቲቱ ከመጡት ጥንታዊያን ቀርጤሳውያንና ግሪኮች የተወለዱ ነበሩ። (የብሉይ ኪዳን ፍልስጤሞች የመነጩት ከዚህ ነው።) የቀርጤስ ሰዎች የሠለጠኑ ሰዎች ሳይሆኑ፥ በጭካኔአቸው፥ ታማኞች ባለመሆናቸውና በስንፍናቸው ይታወቁ ነበር። በዚህ ስፍራ ወንጌልን በጽናት መመሥረቱና መሪዎችን ማስመረጡ የቲቶ ኃላፊነት ነበር። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የአማኞቹን ሕይወት ሊለውጥና የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ የሚያሳዩ ሞዴሎች ሊሆኑ እንደሚገባ አስረድቷል።

ይቀጥላል...

@Grace_Worship
@Grace_Worship