Get Mystery Box with random crypto!

በሕይወት ውጣ ውረድ መካከል ቀና በል/ይ! በሕይወት ውጣ ውረዶች መካከል የሚገጥመን ነገር ብዙ ነ | Gospel

በሕይወት ውጣ ውረድ መካከል ቀና በል/ይ!

በሕይወት ውጣ ውረዶች መካከል የሚገጥመን ነገር ብዙ ነው፡፡ አንዳንዱን ነገር ልንቀበለው፣ እውነት ብለን ልናምነው ሁሉ እንቸገራለን፡፡ ምናልባትም የደረሰው የኾነው ነገር በሙሉ በእኛ ላይ ብቻ የኾነ ያህል ሆኖ ይሰማናል፡፡ የዓለሙን ሁሉ መከራ እኛ የተሸከምን፤ የመከራ ዶፍ በብቸኝነት የወረደብን፤ እግዜሩም ለይቶ እኛ ላይ ብቻ በጠላትነት የዘመተ መስሎ ሁሉ ይሰማናል፡፡

የጓደኛዬ አያት አጭር በሚባል ጊዜ ሴት ልጆቻቸው በተከታታይ ሞቱባቸው፡፡ ሐዘኑ ምን ያህል መሪር እንደሚሆንባቸው ለማሰብ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ የጓደኛዬን እናት ጨምሮ አምስት ልጆች ሞቱባቸው፡፡ ሐዘኑ እንኳን ለእሳቸው ለእኛም እንኳ ከባድ ነበር፡፡

የመጨረሻዋን ልጃቸውን ቀብረን እንደተመለስን ለማጽናናት እስኪቸግር ድረስ ሐዘናቸው መሪር ሆነ፡፡ “ለጉድ ከምታስቀምጠኝ ለምን እኔንስ አትወስደኝም? ምን በድዬህ ነው” እያሉ እሪ ይላሉ፡፡ ለማጽናናት የመጡት ቄስ ብድግ ብለው መስበክ ጀመሩ፤

“የእኔ እናት በመጽሐፍ ቅዱስ ኢዮብ የሚባለው ሰው ልጆቹ ሁሉ በአንድ ጊዜ አለቁበት” ሲሉ የጓደኛዬ አያት “ይተዉኝ አባ አምስት ልጅ በተከታታይ!” ብለው መለሱ፤ አባ ቀበል አድርገው “ኢዮብ ዐሥር ልጅ!” አሉ፡፡

እኛጋ ብቻ የመጣ፣ በእኛ ብቻ የደረሰ የመሰለን መከራ የብዙዎችን በር ያንኳኳ ነው፡፡ በርግጥ በአገር የመጣ ነው እንዴ? ብለን እንደማናቀለው አውቃለሁ፡፡ ግን በቃ ዓለሙ የስብራት ዓለም ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ “ግን ለምን?” ብለን ብንጠይቅ ምላሽ የማናገኝለት ነገር በሕይወታችን ይሆናል፡፡

ይህ የመጣብን የተለየ በደል ፈጽመን፣ ከሰዎች ይልቅ ዐመፃችን ከፍቶም አይደለም፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አምላክ ብቻ ያውቃል፡፡ እንዲነግረንም ደግሞ አይገደድም፤ አምላክ ነዋ፣ ሉዐላዊ አምላክ፡፡ ግን አንድ ነገር መረዳት በጣም ጥሩ ነው፤ እንዲህ ያለ ነገር የገጠመን እኛ ብቻ አይደለንም፡፡

ከሁሉ በላይ በሐዘን ለተሰበሩ ልቦች ጠጋኝ አምላክ አለ፡፡ የሚሠራውን ስለሚያውቅ በእርሱ ልብን ማሳረፍ እጅግ መልካም ነው፡፡ ባልገቡን እና ምላሽ ባላገኘንላቸው ነገር ሁሉ ጌታነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ በእኛ ግርታ ምክንያት ከአምላክነት መንበሩ ዝቅ አይልም፡፡

ዘማሪቷ “ባይገባኝም እንኳ ቅሉ…” እንዳለችው፤ በመልካምነቱ ልብን ማሳረፍ የተገባ ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ከሚገጥሙን ነገሮች የተነሳ የምንሄዳቸው የማይገቡ መንገዶች፣ የምንሰማቸው አታላይ ድምፆች የመጨረሻውን ጸጸት ያበዙታል፡፡

ሸክም ስለሆነብን ነገር ጌታ አምላክን ታምኖ እርሱን ደጅ መጥናት የተገባ ነገር ነው፤ ውጤቱ ምንም ቢሆን፡፡ የመከራን ቀን በአምላክ ጥላ ተሸሽጎ ማለፍን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ደግሞስ እንዲህ ያሉትን የምጥ ቀናት ማን መሸሸጊያ ሊሆን ይችላል፡፡ በመከራስ ቀን ከአምላክ በቀር ሊጠራ የሚችል ማነው? ቢጠራስ ሸክምን አራግፎ እፎይታን ሊሰጥ ማን ይችላል?

ስለዚህም ልብን በአምላክ አበርትቶ እርሱን ሙጥኝ ማለትና ወደ ላይ ቀና ማለት መልካም ነው፡፡ በፊታችን ደግ ቀናት አሉ፡፡ ኢየሱስ ይመጣል! አልያም እኛ ወደ እርሱ እንሄዳለን፡፡ በዚህ እንጽናና!!!

መጋቢ ስንታየሁ በቀለ