Get Mystery Box with random crypto!

ስለ ዮሃንስ ወንጌል እግዚአብሔር ይመስገን የዮሃንስ ወንጌል ልክ እንደ ሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች ኢየ | (✍ GOSPEL TALK ✍)

ስለ ዮሃንስ ወንጌል እግዚአብሔር ይመስገን

የዮሃንስ ወንጌል ልክ እንደ ሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች ኢየሱስን በአመዛኙ ከታሪክ ጋር አጋብቶ ብቻ ሳይሆን የሚነግረን “አሁን” በአማኝ ወይም በቤተክርስትያን ሕይወት ውስጥ ያለውን ፋይዳ በጥልቀት በማውሳትም ነው፡ በሌላ አባባል ታሪካዊ / historical ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን የሚያስተዋውቀን አሁናዊ / existential ክርስቶስንም ነው።

ዮሃንስ በወንጌሉ ከሚገልጻቸው አሁናዊ እውነቶች መካከል አንደኛው አንድነት / unity ነው፡ ይህንን የአንድነት ክቡር እውነት በዋነኛነት በምእራፍ 17 ላይ አጽንኦት በመስጠት ያቀርብልናል።

ክፍሉ የሚጀምረው፦

“ኢየሱስም . . . ወደ ሰማይ አይኖቹን አነሳና እንዲህ አለ”
ብሎ ነው።

ይሄም የሚያሳየን እውነት በዚህ ክፍል ውስጥ ጌታችን የሚናገረው ነገር በሙሉ በአብ ፊት እንደ ጸሎት የቀረበ ምልጃ መሆኑን ነው። በዚህ የምልጃ ምእራፍ ውስጥ ነው እንግዲህ ጌታችን በሚገርምና እጅግ ደስ በሚል መልኩ በአብ፣ በወልድና፣ በአማኞች መካከል ያለውን አንድነት ጸሎታዊ በሆነ ቅርጽ ለአባቱ የሚያቀርበው።

#አንድ
የአማኞች የእርስ በርስ አንድነት

ክርስቶስ በዚህ ምእራፍ ቁጥር አሥራ አንድ ላይ እንዲህ ብሎ ይጸልያል፦

“ቅዱስ አባት ሆይ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው”

መቼም ይህን ቁጥር በጥድፊያ ካላነበብነው በስተቀር ወሳኝ የሆነውን አሳብ የምናልፈው አይመስለኝም፡ ክርስቶስ በዋነኛነት አማኞች እርስ በርስ በአንድ የሰመረ ሕብረት እንዲሆኑ ወይም ብዙዎች ቢሆኑም ነገር ግን አንድ እንዲሆኑ አባቱን ይለምንላቸዋል፡ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ አማኞች አንድ እንዲሆኑ ለማነጻጸሪያ የተጠቀመበት እውነት ነው፡ እንዲህ ይላል፦

“እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ”

የአንድነቱ ንጽረት አባትና ልጅ ናቸው፡ ታዲያ ይሄ አይገርምም!
በዚሁ ወንጌል ውስጥ ጌታችን “እኔና አብ አንድ ነን - We are in one accord” ብሎ እንደተናገረ እናነባለን፣ ይሄንኑ አንድነት ወይም የአሳብና የልብ ስምረት አማኞች እርስ በርሳቸው እንዲለማመዱት ይጸልይላቸዋል፡ እውነት ግን እስኪ አስቡት፣ አብና ወልድ አንድ እንደሆኑት እኛ አንድ እንድንሆን እኮ ነው የሚጸልየው፡ በምድር ላይ የአማኞችን አንድነት ለማነጻጸር የሚመጥን አንድ እውነት ያለው በአብና በኢየሱስ መካከል ያለው አንድነት ብቻ ነው፡ ይሄ አንድነት ደግሞ እኛ #የምንጀምረው ሳይሆን #የምንገባበት ነው፣ ምክንያቱም አስቀድሞ በአባትና በኢየሱስ መካከል የተመሰረተ ነው። አንድነታችን የዘር፣ የቋንቋ፣ የአጥቢያ ቤተክርስትያን፣ የጓደኝነት፣ ወይም የቲፎዞ ሳይሆን የእግዚአብሔርና የኢየሱስ ነው፡ ከዚህ ያነሰ አንድነት በሰው፣ ከሰውና፣ ለሰው የሆነ ነው።

#ሁለት
የአብ፣ የወልድና፣ የአማኞች አንድነት


አማኞች እርስ በርስ ሊኖራቸው ከሚገባቸው አንድነት ወይም ሕብረት በዘለለ መልኩ ጌታችን፣ እርሱ፣ አብና፣ አማኞች ደግሞ በአንድ አንድ እንዲሆኑ ሲጸልይ እናነባለን ቁጥር 21 - 22

“አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ፣ እኔም በአንተ፣ እነርሱም ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ . . . እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ . . . “

ደቀመዛሙርት በአብና በወልድ መካከል ባለ አንድነት እርስ በርሳቸው አንድ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን የተጸለየላቸው፣ እነርሱ ራሳቸው ከአብና ከወልድ ጋር በአንድ እንዲሰመሩም ጭምር ነው፡ አብ በወልድ ውስጥ፣ ወልድ ደግሞ በአብ ውስጥ፣ አማኞች ደግሞ በአብም በወልድም ውስጥ ሆነው በአንድ እንዲሆኑ፡ እውነት ከዚህ የሚበልጥ ጸሎት አለ? እውነት ከዚህ የሚበልጥ ክብር ወይም ሕይወት አለ? ከአብና ከወልድ ጋር አንድ መሆን!!

#ማሳረጊያ

የእርስ በርስ አንድነታችን ወይም ሕብረታችን በአብና በወልድ መካከል ባለው ሕብረት መቃኘቱ ሲገባን፣ እንዲሁም አንድነታችን የእርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን ከአብና ከወልድም ጋር በአንድ መሆኑ ሲገባን፣ ለዚህ ክቡር እውነት ስንል የማንጥለው ነገር አይኖርም፡ ለዚህ ሕብረት ብለን የምንጥለው ነገር ሕብረቱ የገባንን ያህል ነው።

በዚህ አንድነት ውስጥ ያልተሰመረ ሁሉ፣ ፓስተር ይሁን ሐዋርያ፣ ወንጌላዊ ይሁን ነብይ፣ የሥነ-መለኮት ምሁር ይሁን ዓቃቤ-እምነት፣ ፈጽሞ የመለኮትን ሕይወት አይቋደስም - የመለኮት ሕይወት ከአብና ከወልድ ጋር እንዲሁም እርስ በርስ አንድ በመሆን ብቻ የሚገለጥ ነው።

ምን አይነት ክብር ነው!
ከአብም ከወልድም ጋር በአንድ መሰመር!


“ኅብረታችንም ከአባት ጋር ክልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው”

Yilu danu
@nazrawi_tube
@nazrawi_tube