Get Mystery Box with random crypto!

~ ነቢዩላህ ኢብራሒም እና ልጃቸው እስማኢል.... 'እንደዚሁም ኢብራሒምን (እንዲያውቅና) ከአረጋ | ወርቃማ ንግግሮች

~ ነቢዩላህ ኢብራሒም እና
ልጃቸው እስማኢል....

"እንደዚሁም ኢብራሒምን (እንዲያውቅና) ከአረጋጋጮቹም ይኾን ዘንድ የሰማያትንና የምድርን መስኮት አሳየነው።" (አል አንዓም፡75)

ከላይ የተወሳውን የቁርአን አንቀጽ አስመልክቶ በተላለፈ ዘገባ ኢብራሒም (ዐ ሰ) በእያንዳንዷ ሌሊት ወደ ሰማይ ይወጡ ነበር። ወደ ሰማይ ዘልቀው በወጡባት አንድ ሌሊት ኃጢያት የሚሰራው ሰው ተመለከቱ እና እንዲህ አሉ፦

"ጌታዬ ሆይ! ይህ ሰው ከረዘቅከው ይበላል። በሰጠኸው እግሮች ይራመዳል። ይህ ሆኖ ሳለ ትዕዛዝህን ግን አይፈፅምም፣ አጥፋው!"

ያን ሰው አላህ ሱ ወ አጠፋው። ኢብራሒም (ዐ ሰ) ሌላ ወንጀል ፈፃሚ ሲያዩ አሁንም ዱዓ አደረጉበት። ከአላህ ጥሪ መጣላቸው።

" ኢብራሒም ሆይ! ባሮቼ እንዲጠፉ ከምታደርገው ዱዓ ታቀብ!" በሂደት እንዲስተካከሉ ቀስ አድርገህ ያዛቸው! እኔ በየዕለቱ ወንጀል ሲፈፅሙ እመለከታለሁ። ነገር ግን አላጠፋቸውም!"

ኢብራሒም (ዐ ሰ) ወደ መሬት ሲመለሱ በቁርአን የተወሳችውን ህልም ያያሉ። ልጃቸው በሙሉ ፍቃደኝነት "አባቴ! የታዘዝከውን ፈፅም" ሲላቸው የአላህ ወዳጅ ልጃቸውን ለማረድ ተዘጋጁ። ቢላዋውን በእጃቸው ይዘው ወደ አላህ እንዲህ በማለት ተጣሩ፦

"አምላኬ ሆይ! ይህ ብቸኛ ልጄ ነው። የዓይኔ ማረፊያ፣ የልቤ ፍቅር ነው።"

አላህ (ሱ ወ) እንዲህ ሲላቸው ሰሙ፦

"ባሪያዬን እንዳጠፋ የተማፀንክባትን ሌሊት ታስታውሳለህ? አንተ ለልጅህ እንደምታዝነው፣ እኔም ለባሪያዬ እጅግ በጣም አዛኝ፣ እጅግ በጣም ሩኅሩኅ መሆኔን አታውቅምን? አንተ ባሪያዬን እንዳጠፋ ተማፀንከኝ። (ስለዚህ) አሁን ልጅህን እንድትሰዋ እፈልጋለሁ!" ሱብሀነሏህ ውድ አንባቢያን አላህ (ሱ ወ) ልክ ልጃችን አንዳች ነገር ሲሆንብን እንደምንጨነቀው እንደምናዝነው ሁሉ አላህ (ሱ ወ) ደግሞ ለባሪያዎቹ የበለጥ ምን ያክል ሩህሩህ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል።

ኢስማዒል (ዐ ሰ) የመታረጃ ጊዜያቸው ሲቃረብ አባታቸውን እንዲህ በማለት መከሩ፦_

1 = እጆቼን እና እግሮቼን አጥብቀህ እሰራቸው።ስቃይ ሲበዛብኝ እንዳላስቸግርህ እና የጌታዬን መብት እንዳላጓድል (ይረዳኛል)።_

2 = ደሜ እንዳይረጭብህ ልብሶችህን በደንብ ሰብስብ።_

3 = ቢላዋውን በደንብ ሳለው። ነፍሴ በቶሎ እንድትወጣ፣ አንተም ቶሎ እንድትገላገል።_

4 = ቢላዋውን ይዘህ ወደ ፌቴ አትመልከት፣ የአባትነት አንጀት የታዘዝከውን ከመፈፀም እንዳያዘገይህ።_

5 = ልብሴን ይዘህ ወደ እናቴ ሒድ! ለመፅናናት ይረዳት ይሆናል! "ልጅሽ ሸፊዕ ሆኖ ወደ አላህ ሔዷል" በላት።"


ኢብራሒም (ዐ ሰ) እነዚህን ቃላት ከልጃቸው አንደበት ሲሰሙ ዓይኖቻቸው በእንባ ተሞሉ። አብዝተው አለቀሱ። እንዲህም አሉ፦

"የአላህን ትዕዛዝ እንድፈፅም ምን ያክል አገዝከኝ!" ቀጥለው እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንስተው ዱዓ አደረጉ፦

"ጌታዬ! ባለሁበት ሁኔታ ትዕግስትን አላብሰኝ! እንግዲህ ምንም አልቀረኝም። አርጅቻለሁና እዘንልኝ!"

ኢስማዒልም (ዐ ሰ) አሉ፦ "ጌታዬ! ትዕግስትን እና ፅናትን አላብሰኝ!። አባቴ ሆይ! የጀነት በሮች ተከፍተዋል።"

መላኢካዎች በነገሩ ግራ ተጋብተውና ተደናግሯቸው ሱጁድ በመውረድ አላህን ይማፀናሉ፦ "ጌታችን ሆይ! ነቢይህ ያንተን ፍቃድ ሊሞላ ለመሰዋዕት ተጋድሟል፣…እዘንላቸው።" ይላሉ።

ኢስማዒል ቀጠሉና ለአባታቸው ፍፁም ታዛዥነታቸውን ለመግለፅ፣ ፅናታቸውን ለማሳየት እንዲህ አሉ፦

"አባቴ! ከፍቅር ማሳያዎች አንዱ አለመዘግየት ነው! በላ የታዘዝከውን ቶሎ ፈፅም!"

ኢብራሒም (ዐ ሰ) ኢስማዒልን (ዐ ሰ) አጋድመው "ውድ ልጄ! እንግዲህ የውመል ቂያማ ላይ እንገናኝ! በትንሳኤው ቀን ዳግም አይሃለሁ!" አሉትና ቢላዋውን አጥብቀው ይዘው ወደ ኢስማዒል (ዐ ሰ) አንገት ሰነዘሩ። በዚያችው ቅፅበት አላህ (ሱ ወ) ጅብሪልን አዘዘው፦

"ፍጠን። ቢላዋውን ገልብጠው!" ጅብሪል ቢላዋው የኢስማዒልን (ዐ ሰ) አንገት ከመንካቱ ገለበጠው። ኢብራሒም (ዐ ሰ) እንደገና ቢላዋውን አጥብቀው ይዘው ለመሰንዘር ሞከሩ። ግን መቁረጥ አልቻሉም። ቢላዋው እጃቸው ላይ እንዳለ ተገለበጠ።

~ አላህ (ሱ ወ) እንዲህ አለ፦

~ "ኢብራሒም (ዐ ሰ) ራዕዩን ተቀብሏል። ከልብ ማመኑን አረጋግጧል" ቀጠለና በአላህ (ሱ ወ) ትዕዛዝ መሰረት ጅብሪል ተክቢራ እያደረገ የጀነት በግ ይዞ ከተፍ አለ።

~ «አላሁ አክበር አላሁ አክበር»

ኢብራሒም (ዐ ሰ) ተክቢራውን ሲሰሙ እንዲህ በማለት ተቀበሉት፦

~ «ላኢላሀ ኢልለሏህ ወላሁ አክበር»

~ ኢስማዒልም (ዐ ሰ) እንዲህ በማለት ተክቢራውን ሞሉት፦

~ «አላሁ አክበር ወሊላሒል ሐምድ»

በዚህ መልኩ የተክቢር አትተሽሪቅ ክፍሎች ተሟሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ዒድ አል አድሓ (የመስዋዕቱ በዓል) በመጣ ቁጥር በዓሉ ከዋለበት ቀን ንጋት ላይ ጀምሮ እስከ አራተኛው ቀን የዐስር ወቅት ድረስ ተክቢር አትተሽሪቅ ይባላል።

አባት እና ልጅ በደስታ ተሞልተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እናታችን ሐጀር ኢስማዒልን (ዐ ሰ) እቅፏ ውስጥ አስገባችው። ወደ ደረቷ በኃይል አስጠጋችው።

~ ~
https://t.me/Golden_Speech
https://t.me/Golden_Speech