Get Mystery Box with random crypto!

ለቅዱስነታቸው የተያዘው ጸሎት በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ቅዱስነታቸውን መድኃኔዓለ | ጎዶልያስ ቲዩብ - Godoliyas Tube

ለቅዱስነታቸው የተያዘው ጸሎት
በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስነታቸውን መድኃኔዓለም ፈውሱን ሰጥቶ ወደ መንበራቸው በሰላም ይመልስልን።

በታሪካዊው የቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ያየሁት አርማ ነው የለጠፍኩት ትላንትና ለገዳማችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማየት በሄድኩበት ሰዓት ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ስገባ የተመለከትኩት ነው።

በሁለቱም የቤተ ክርስቲያኑ በሮች ከተዘረጋው ባንዲራና ቤተ ክርስቲያኑን ካሸበረቀው የባንዲራ ዲኮር ከፍ ብሎ የቤተ ክርስቲያን ርዕሰ መንበር የሆኑትን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ፎቶ በትላልቅ ባነሮች በሚያምር መልኩ ተዘጋጅቶ አየሁ።

በባነሩ ራስጌ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ይላል
በባነሩ ግርጌ
ከህመምዎ ድነው ወደ መንበረ ክብርዎ እንዲመለሱ ቤተ ክርስቲያን እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆችዎ እንጸልያለን ይላል።
ደስ አለኝ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለአባቶቻቸው ዋጋ ይከፍላሉ

ስመለከተው ቅዱስነታቸውን አሰብኳቸው አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ አሉ ይሆን ከሄዱባት ቅጽበት ጀምሮ አሜሪካ ለህክምና ሄደው በሰላም እንደደረሱ ሰማን።

አሁን ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ግን ማንም የነገረን የለም ሚድያውና ዩቲበሮች የሆነውና ያልሆነውን ዘባርቀው ሐሳብ ውስጥ ከተቱን እንጂ አንዳችም አሁን ስላሉበት ደረጃ ሊነግሩን አልፈለጉም።

የE.O.T.c ሚድያ
የማህበረ ቅዱሳን ሚድያ
በጣም ይገርማል በየዕለቱ እየተከታተሉ ቅዱስነታቸው ያሉበትን ሁኔታ የት እየታከሙ እንደሆነ ሊነግሩን ይገባ ነበረ አልተነገረንም የቅዱስ ፓትርያርኩ ጉዳይ የመላው የኦርቶዶክሳውያን ጉዳይ ነው

በረከታቸው ይድረሰን ብፁዕ አቡነ አብርሃም
ጊዜ ሁኔታ ሰዓት ተመቻቸልኝ ያለው ሁሉ ባልተገባ መንገድ በቅዱስነታቸው ላይ ሲናገር በአጭር ጊዜ ከሀገረ ስብከታቸው በአስቸኳይ መጥተው የሚያሳርፍ መልስ በግላጭ ሰጥተው በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚነገሩ ያልተገቡ ንግግሮች ሁሉ በቤተ ክርስቲያን እንደ ተነገሩ እንቆጥራቸዋለን ስለዚ እያሰባችሁ ተናገሩ በይሆናል እየተናገራችሁ ቤተ ክርስቲያንን አትጉዷት ብለው የማያዳግም መልስ ስጥተዋል በረከታቸው ይድረሰን።

ሚድያዎች ባይናገሩም ባሉበት ሆነው በመንፈስ ይመለከቱናል እኛም ልጆቻቸው በጸሎት እያሰብናቸው ነው ብለው በውስጥ ያለውን የልጅነት ፍቅራቸውና በጸሎት እያሰቧቸው እንደሆነ የቅዱስ ዑራኤል ልጆች አስመስክረዋል።

ሌሎቻችንስ እያሰብናቸው ይሆን በእያንዳንዷ ጸሎታችን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ርዕሰ መንበር ልንጸልይ ይገባል።

በርግጥ በቤተ ክርስቲያናችን ጸልዩ በእንተ ርእሰ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ማትያስ ትላለች አሁን ደግሞ በተለየ መንገድ ሁላችንም በጾማችን በጸሎታችን ልናሳስባቸው ይገባል።

የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችና ሰንበት ትምህርት ቤትን ግን ሳላመሰግን አላልፍም አርአያነታችሁን ገልጣችኋልና እናመሰግናለን።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚድያዎች አሁንም ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ እንድትገልፁልን እንፈልጋለን።

የቅዱስነታቸው በረከት አይለየን በሰላም በጤና ይመለሱልን

ጸልዩ በእንተ ርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ማትያስ ወበእንተ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ወበእንተ ብፁዕ አቡነ ዮናስ ወበእንተ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ

ስለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ አባ ማትያስ
ስለ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ
ስለ ብፁዕ አቡነ ዮናስ
ስለ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጸልዩ

ጸልዩ በእንተ ሰላም
ስለ ሰላም እንጸልይ
ስለ ቤተ ክርስቲያን እንጸልይ
ስለ ሚራቡ ስለ ሚጨነቁ እንጸልይ
ስለ ታመሙት በየ ሆስፒታሉ በየጸበሉ በመከራ በጭንቅ ስላሉት እንጸልይ
ያለበደላቸው ያለ ኃጢአታቸው ደማቸው አየፈሰሰ ስላሉ ንፁሃን እንጸልይ አምላከ ሰላም ሰላሙን ይስጠን

አባ አትናቴዎስ ወልደ ጎርጎርዮስ
አዲስ አበባ 26/11/2014