Get Mystery Box with random crypto!

+ ዝክረ ቅዱስ ዮሐንስ + ............................................ | ግጻዌ

+ ዝክረ ቅዱስ ዮሐንስ +
................................................................
አምላካችን ክርስቶስ ፍጥረቱን ሁሉ ይወዳል። ከፍጥረታቱ ሁሉ ደግሞ አስበልጦ ሰውን ይወዳል። ከሰውም ሁሉ ደግሞ ድንግል ማርያምን ይወዳታል፤ ምክንያቱም አማናዊት መቅደሱ፣ ማሕጸኗን ዙፋኑ አድርጎ ከእርሷ ተወልዶ እናቴ ሊላት ወዷልና። ከእናቱ ቀጥሎ ደግሞ እሷን አደራ ብሎ የሰጠውን ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ዮሐንስን ይወዳል። አሃ? እንዴት ነው ታዲያ እግዚአብሔር ሲወድ ያዳላል ማለት ነው? አያዳላም!

አባቶቻችን ሲያስተምሩ የእግዚአብሔር ፍቅር ልክ እንደ ጸሐይ ብርሐን ነው ይላሉ። ጸሐይ ስትወጣ እኩል ለሁሉም ብርሃኗን እንደምትሰጥ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍቅርም ለሁሉም እኩል ነው። ነገር ግን የምናገኘው የጸሐይ ብርሃን የሚወሰነው የቤታችንን መስኮት በከፈትነው ልክ ነው። ሙሉ ለሙሉ ከዘጋነውና ከቤት አንወጣም ብለን ቁጭ ካልን የጸሐይ ብርሃንን ጭራሽ ላናይ እንችላለን። የእግዚአብሔር ፍቅርም የልባችንን መስኮት በከፈትነው ልክ ይገባል። ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስም ለእግዚአብሔር ፍቅር የልቡን በር አንዳች ሳያስቀር ብርግድ አድርጎ የከፈተ ንዑድ ሐዋርያ ነው። ለዚህም በጻፈው ወንጌል ላይ በተለያዩ ቦታዎች "ኢየሱስ ይወደው የነበረው ሐዋርያ" እያሉ ራሱን ሲገልጽ እናየዋለን።

አንድ ሰው ሲሞት እጅግ የሚወደው ዘመድ ወይም ሀብት ካለው አደራ ብሎ የሚሰጠው ከልቡ ለሚያፈቅረውና ለሚያምንበት ሰው እንደሆነ ሁሉ ጌታችንም በመስቀል ሆኖ ብቸኛ ቤቱም፣ መቅደሱም፣ ዘመዱም፣ ፍጥረቱ ሆና እናትም የሆነችውን ለሚወደውና ለሚያምንበት ዮሐንስ አስረከባት። እኛም እናታችን እንድንላት በዮሐንስ በኩል ተሰጠችን። "ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው" እንዲል ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ ለእኛ ሲል መሞቱ የፍቅሩን ጥግ ለእኛ ያሳየበት የመጀመሪያው ነገር ነው። ከዚያ ቀጥሎ ግን ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያለውን ታላቅ ፍቅሩን ያየነው እናቱን እንኳን ሳይሰስት "እናንተም እንደእኔ እናቴ በሏት" ብሎ በዮሐንስ በኩል ሲሰጠን ነው። ታዲያ ለዚህ ክቡር ድንግል ሐዋርያ ምን ያህል ውለታ ይኖርብን ይሆን?

ቅዱስ ዮሐንስ "ኢየሱስ ይወደው የነበረ ሐዋርያ" ብቻም ሳይሆን እርሱም አምላኩን ከልቡ የሚወድ ነበር። ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ወንድሞቹ ሐዋርያት ሲሸሹ ፍቅር ፍርሐትን አውጥታ ትጥላለችና እስከ መስቀል ስር ድረስ በፍቅሩ ጽንዓት ምክንያት የተከተለ ነበር። ጌታ የተቀበለውን መከራም ካየ በኋላ "ቁጹረ ገጽ .. ፊቱ የተቋጠረ" ተብሎ ስም እስኪወጣለት ድረስ ሕማሙን እያሰበ በኃዘንና በለቅሶ የኖረ ጻድቅ ሐዋርያ ነበር።

"ተውህቦ መራኁት ለአቡነ ጴጥሮስ፣ ወድንግልና ለዮሐንስ፣ ወመልዕክት ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን" ብለን በቅዳሴያችን እንደምናዜመው ለቅዱስ ዮሐንስ ድንግልና ተሰጥቶታል። የጌታን መታጠቂያ በአንድ ቀን ታጥቆ ፍትወቱ ከእርሱ ፍጹም ተወግዶለታል። (በነገራችን ላይ ወንጌለ ዮሐንስን የሚጸልይ ወይም የሚደግም ሰው የዝሙት ፈተና ይወገድለታል ይላሉ አባቶቻችን) ሕይወቱን ሙሉ በንጽሕና፣ በድንግልና የኖረ ጻድቅ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ ነው።

ከሶስቱ የምሥጢር ሐዋርያት አንዱ የሆነው ሊቁ ዮሐንስ የፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስን ፍቅሩን እንደሞቀው ሁሉ ብርሃኑን ደግሞ በደብረ ታቦር አይቷል። ጌታ በአንድ ወቅት ሐዋርያቱን "ሰዎች ማን ይሉኛል" ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ "አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ" ብሎ ሲመሰክር ክርስቶስ መልሶ " በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህም" ብሎት ነበር። ቅዱስ ዮሐንስም ይህን ሲሰማ የሥላሴን ነገር የሚገልጠው አብ እንደሆነ በዚህ ተረድቶ ከጌታ ደረት ተጠግቶ የወልድ ልቡ ከሚሆን ከአብ የሥላሴን ምሥጢር በቅጽበት ሰምቶ "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ" ብሎ ወንጌሉን መጻፍ ጀመረ።

ይህ ምሥጢረኛ ሊቅ ከጌታ ደረት መጠጋቱ ሳያንስ ሠላሳ ዓመት ሙሉ ከልጇ ስትማር ከነበረችው ልህቅተ ሊቃውንት የምሥጢር መዝገብ እመቤታችን ጋርም አሥራ አምስት ዓመት እንደ ልጇ እየታዘዛት ሲማር ኖሯል። ታዲያ የዚህን ንዑድ ክቡር ሐዋርያ ክብር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? ክብሩ ከመላዕክት ጋር ስለተካከለ ለመልዓክ እንኳን ሊሰግድ ሲሞክር መልዓኩ ልክ እንደ አባቶቻችን "ኧረ አይገባም" ብሎ በክብር ያስቆመውን አባት ማክበርስ በጌታ ዘንድ ምን ያህል ያስከብር ይሆን? ይህን "ኢየሱስ ይወደው የነበረው ሐዋርያን" መዘከርስ በኢየሱስ ዘንድ ምን ያህል ያስወድድ ይሆን?

እንግዲህ ምን እንላለን? እንደ ውዱ አባታችን ለክርስቶስ ፍቅር ልባችንን ውልል አድርገን የምንከፍትበት ብርታት፣ እስከ መስቀል ሥር የምንከተልበት ፍቅርና ጽንዓት፣ ተከትለንም ክብርት እናቱን የምንረከብበት ንጽሕና ለሁላችን ያድለን። የንዑድ ክቡር ቅዱስ ዮሐንስም ረድኤቱ፣ በረከቱ፣ ጸሎቱ፣ ፍቅሩ ሁላችንን ትርዳን። አሜን!

ዲያቆን ዮሐንስ ደረጀ
2015 ዓ.ም ጥቅምት አቦ ማህሌት ላይ ተጻፈ
አዲስ አበባ
https://t.me/dnJohannes

@dnJohannes
@dnJohannes 
@dnJohannes 
@dnJohannes