Get Mystery Box with random crypto!

#ስንክሳር_ዘሰኔ_16 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ | ግጻዌ

#ስንክሳር_ዘሰኔ_16


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰኔ ዐሥራ ስድስት በዚህች ዕለት መልካም ሽምግልና ያለው ስም አጠራሩ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ አባት የላይኛው ግብጽ ሰው #አባ_አቡናፍር አረፈ፡፡

የዚህንም አባት ገድል የተናገረ አባ በፍኑትዮስ ነበር እርሱ ቁጥሩ ከገዳማውያን ነውና፡፡

አባ በፍኑትዮስም ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ዛፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ፡፡

በአንዲት ዕለትም አባ በፍኑትዮስ ወደርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍርን አየው ፈርቶም ደነገጠ የሰይጣን ምትሐት የሚያይ መስሎታልና ይህም አባት አቡናፍር ልብስ አልነበረውም ጸጉሩና ጽሕሙ ሥጋውን ሁሉ ይሸፍናሉ አባ በፍኑትዮስንም በላዩ በመስቀል ምልክት አማትቦ አጽናናው በፊቱም አቡነ ዘበሰማያትን ጸለየ ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው አለው ይህንንም በማለቱ ከእርሱ ፍርሃቱን አራቀለት፡፡

ከዚህ በኋላ ሁለቱም በአንድነት ጸለዩ የእግዚአብሔርንም ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ፡፡

ከዚህም በኋላ ወደዚህ በረሀ ከዓለም አወጣጡ እንዴት እንደሆነ በዚያም በረሃ አኗኗሩ እንዴት እንደሆነ ይነግረው ዘንድ አባ በፍኑትዮስ አባ አቡናፍርን ለመነው፡፡

አባ አቡናፍርም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ደጋጎች ዕውነተኞች መነኮሳት በሚኖሩበት በአንድ ገዳም እኖር ነበር የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኑአቸውም ሰማሁ እኔም ከእናንተ የሚሻሉ አሉን አልኳቸው እነርሱም አዎን እነርሱ በበረሀ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን በበረሀ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው አሉኝ፡፡

ይህንንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልቤ እንደ እሳት ነደደ መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ የፈቀደውን ይመራኝ ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ተነሥቼ ጸለይኩ፡፡ ትንሽ እንጀራም ይዤ ተጓዝኩ አንድ ጻድቅ ሰውም አግኝቼ የገዳማውያንን ገድላቸውንና ኑሮአቸውን እያስተማረኝ በእርሱ ዘንድ ኖርኩ፡፡

ከዚህም በኋላ ወደዚህ ደረስኩ እግዚአብሔርም ያዘጋጀልኝን ይቺን ሰሌን አገኘኋት በየዓመቱም ዐሥራ ሁለት ዘለላ ታፈራለች ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚህች ምንጭ እጠጣለሁ በዚህችም በረሀ እስከ ዛሬ ስልሳ ዓመት ኖርኩ ከቶ ያላንተ የሰው ፊት አላየሁም አለኝ፡፡

ይህንንም ሲነጋገሩ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ ወረደ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ሰጣቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ከሰሌን ፍሬ ጥቂት ምግብ ተመገቡ፡፡

ያን ጊዜም የቅዱስ አባ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ እንደ እሳትም ሆነ በእግዚአብሔርም ፊት ተንበርክኮ ሰገደ ለአባ በፍኑትዮስም ሰላምታ ሰጠው ያን ጊዜም ነፍሱን በጌታ እጅ ሰጠ፡፡ ቅዱስ በፍኑትዮስም በጸጉር ልብስ ገንዞ በዚያች ቦታ ቀበረው፡፡

ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ አሰበ በዚያን ጊዜ ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች የውኃውም ምንጭ ደረቀ፡፡

ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የቅዱስ አባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ የከበሩ ገዳማውያን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡


ዳግመኛም በዚህች ዕለት የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለት ሕፃኑንና እናቱንም ይዞ ወደ እስራኤል አገር እንዲመለስ አዘዘው፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ስለ እናቱ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መከራና ስደት ይቅር ይበለን ለዘላለሙ አሜን፡፡





@gitsawe
@gitsawe
@gitsawe
@gitsawe