2020-10-27 16:51:30
ካለምክ አይቀር ትልቅ ሕልም ይኑርህ!!!
“ቺክን ሱፕ ፎር ዘ ሶል” ("Chicken Soup For the Soul") ዝነኛ መጽሃፉ ላይ ጃክ ካንፊልድ (Jack Canfield) አንድን አስገራሚ እውነተኛ ታሪክ አስፍሯል፡፡ በካሊፎንያ ግዛት ውስጥ ሳን ሲድሮ በተሰኘ ስፍራ አንድ ሞንቴ ሮበርትስ (Monty Roberts) የተባለ ሰው ትልቅ ፈረስ የሚያረባበትና የሚያሰለጥንበት እርሻ አለው፡፡ የዚህ ባለሃብት ጅማሬ ድንቅ ታሪክን ያዘለ ነው፡፡
የሞንቴ አባት ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ፈረሶችን በማሰልጠን የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ የሞንቴም ሕይወት ወዲህና ወዲያ ከሚዘዋወር አባቱ ጋር የተቆራኘ ስለነበር ትምህርት ቤቱን በማቋረጥ ደጋግሞ ከአባቱ ጋር ይዘዋወር ነበር፡፡
አንድ ጊዜ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ሳለ አስተማሪያቸው ወደፊት መሆን የሚፈልጉትን ሕልማቸውን በጽሑፍ አቀናብረው እንዲመጡ የቤት ስራ ሰጣቸው፡፡
ሞንቴ ማታ እቤቱ በመግባት ሰባት ገጽ ሙሉ ወደፊት ማድረግና መሆን ስለሚፈልገው ነገር ጻፈ፡፡ ወደፊት የፈረስ እርባታና ማሰልጠኛ ያቀፈ ትልቅ እርሻ እንዲኖረው እንደሚፈልግና ያንንም ግቡን የሚገልጽ ጽሑፍ ነበር፡፡ ከዚህ ግቡ ጋር የእርሻውን ንድፍ በስእል መልክ በማስፈር ለተመልካቹ ግልጽ በሆነ መልኩ አስፍሮት ነበር፡፡ ከ80 ሄክታር ያላነሰ ስፍራን አልሞ ነበር፡፡ ይህ ሕልም ቀድሞውኑ በውስጡ ሲብላላ የነበረ ጉዳይ ስለነበረ ጊዜን ሰጥቶትና በጥራት በመስራት በሚቀጥለው ቀን ለአስተማሪ አስረከበው፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላ ውጤት የያዘውን ወረቀቱን አገኘ፡፡ በወረቀቱ ፊት ለፊት ገጽ ላይ በቀይ “F” ተጽፎበታል፡፡ ከውጤቱ በታች ደግሞ፣ “ክፍለ ጊዜው ሲያልቅ ወደ ኋላ ቀርተህ አነጋግረኝ” ይላል፡፡
ሕልመኛው ሞንቴ ከክፍለ ጊዜው በኋላ አስተማሪውን ለማግኘት ሄደ፡፡ ገና አስተማሪውን እንዳገኘው፣ “F ያገኘሁት ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው፡፡ አስተማሪውም በመመለስ፣ “እንዳንተ ላለ ወጣት ይህ ሕልም ትንሽ ቅጥ ያጣ ነው፡፡ ገንዘብ የለህም፣ ኑሮን ለመግፋት ወዲህና ወዲያ በመዞር የሚሰራ ቤተሰብ ነው ያለህ፡፡ ባጭሩ ምንም ነገር የለህም፡፡ የፈረስ ማርቢያ እርሻ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ መሬት መግዛት አለብህ፣ እርባታውን ለመጀመር ቅድመ ክፍያ ያስፈልግሃል፣ ለእርባታ የሚሆኑ ፈረሶችን ለማግኘት ገንዘብ ይጠይቅሃል” በማለት ሕልሙ ላይ መድረስ የማይችልበትን የምክንያት አይነት ደረደረለት፡፡ በመጨመርም፣ “ይህንን ምኞትህን እውን ልታደርግበት የምትችልበት ምንም መንገድ ሊኖር አይችልም፡፡ ቀለል ያለ ግብን ጽፈህ ከመጣህ የሰጠሁህን ውጠት አሻሽልልሃለሁ” በማለት ወረቀቱን ሰጠው፡፡
ሞንቴ እቤቱ በመሄድ አስተማሪው የነገረውን ነገር ለረጅም ጊዜ ቁጭ ብሉ በጣም አሰበበት፡፡ አባቱንም ሃሳብ እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ የአባቱ መልስ፣ “ልጄ ሆይ፣ በጉዳዩ ላይ የራስህን አመለካከት መወሰን አለብህ፡፡ ሆኖም፣ ይህ የምትወስነው ውሳኔ በጣም አስፈላጊ ውሳኔ እንደሆነ አስባለሁ” የሚል ነበር፡፡
ሞንቴ በነገሩ ላይ ለአንድ ሳምንት ብዙ ካሰበበት በኋላ ያንኑ ወረቀት ለአስተማሪው መለሰለት፡፡ በወረቀቱ ላይ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፣ “ለቤት ስራዬ የሰጠኸኝን የ F ውጤት ከአንተ ጋር አቆየው፣ እኔ ከሕልሜ ጋር እቆያለሁ”፡፡
ይህ ታሪክ ከተከሰተ ከብዙ አመታት በኋላ በአሁን ጊዜ ሞንቴ ሮበርትስ በ80 ሄክታር ላይ ያረፈ ትልቅ የፈረስ ማርቢያ እርሻ አለው፡፡ በዚያም እርሻ ውስጥ 370 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የግል መኖሪያ አለው፡፡ ያንን F ያገኘበትንና ሕልሙ የተጻፈበትን ወረቀት በፍሬም አድርጎ በሳሎን ቤቱ ግድግዳ ላይ ሰቅሎታል፡፡ ሞንቴ በውስጡ የነበረውንና ከልቡ ያመነበትን ሕልም ከአስተማሪው የግል አመለካከት የተነሳ ለመጣል እምቢ ያለ ሰው ነበር፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሞንቴ እና በአለማችን የሚገኙ ሌሎች በርካታ እሱን መሰል ሰዎች በተለያዩ ሁኔታዎችና ሰዎች፣ “ከዚህ ማለፍ አትችሉም” በመባል የተሰመረባቸውን የገደብ መስመር አልፎ ለመሄድ የቆረጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎች ከራሳቸው እይታ በመነሳት ማድረግ ወይም መሆን የምንችለውንና የማንችለውን የመገመት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ በዚያ ገደብ ውስጥ የመቆየትና ያለመቆየት ውሳኔው ያለው ግን እኛው ጋር ነው፡፡ “አይቻልም” ሲሉን በውስጣችን “ይቻላል” በማለት፤ “ያንተ ነገር አከተመ” ሲሉን ለራሳችን “የእኔ ነገር አላከተመም” እያልን በመንገር ወደፊት የመገስገስ ሙሉ መብትና ብቃቱም አለን፡፡ በሌላ አባባል፣ ሊገታን የሚችል ገደብ እኛው ያበጀነው ገደብ ነው፡፡
የይቻላል እይታ ማለት በአንድ ሙከራ ሳንገታና ሰዎችና ሁኔታዎች በሚሰጡን “አትችልም” የሚል መልእክት ሳንገደብ ወደ ፊት ለመገስገስና የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ አላማችን ጋር ለመድረስ መትጋት ማለት ነው፡፡ ሆኖም፣ አብዛኛውን ጊዜ አንድን ነገር ለማከናወን ሁሉ ነገር የተሟላልን አይነት ሰዎች መሆን እንዳለብን እንድናስብና ቀድሞውኑ ተስፋ ቆርጠን እንቀመጣለን፡፡ በሕይወታችን ግን ስኬታማ ለመሆን ሁሉ ነገር የተሟላ መሆን የለበትም፤ ያመንንበትን መልካም ዓላማ ለመከተል ውስጣችን ሙሉ መሆን ነው ያለበት፡፡ ይቻላል!!!
(እይታ ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ ውስጥ የተወሰደ)፡፡
4.6K viewsBĺªçķ ✟✞ ⒶⓃ, 13:51