Get Mystery Box with random crypto!

+ ዘኬዎስ አጭር ባይሆን + ዘኬዎስ በማጠሩ ምክንያት በኢያሪኮ እያለፈ ያለውን ክርስቶስን ለማየት | ጋሻ ƬƲƁЄ ꍟ꓄ꃅꀤꂦᖘꀤꍏ

+ ዘኬዎስ አጭር ባይሆን +

ዘኬዎስ በማጠሩ ምክንያት በኢያሪኮ እያለፈ ያለውን ክርስቶስን ለማየት ተቸገረ:: ሕዝቡ ብዙ ነውና የቆሙት ሁሉ ጌታን ከማየት ከለሉት:: የሾላ ዛፍ ላይ ወጥቶ ጌታን ለማየት ሲሞክር ጌታ አሻቅቦ አየው::

እሱ ዛፍ ላይ ጌታን ሊያይ እንጂ ሊታይ አልወጣም:: ጌታ ሊታዩ ከሚሞክሩ ይልቅ ሊያዩት የሚሹትን ይወዳልና ዘኬዎስን ጠራው::

ከምድር ቆመን ዓይናችንን አንጋጥጠን ማረን የምንለው ጌታ ዘኬዎስን ከምድር ሆኖ ወደ ላይ እያየ ና ልማርህ አለው:: "ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛል" አለው:: ጌታ ወደ ቤቱ ገባ:: ለዘኬዎስ ቤት መዳን ሆነለት::

ዘኬዎስ አጭር ባይሆን ኖሮ ከሰዎች ጋር እየተጋፋ ጌታን ያይ ይሆናል እንጂ በጌታው ዓይን ለመታየት የሚያበቃ ትጋት አያሳይም ነበር:: ምናልባትም ሰዎችን ገለል በሉ እያለ በኩራት ሲጋፋ ከአንዱ ጋር ሲጣላ ሊቆይ ይችል ነበር::

ዘኬዎስ አጭር ባይሆን ከዛፍ ላይ አይወጣም ነበር:: 
ዘኬዎስ አጭር ባይሆን የሠራዊት አምላክ ወደ ቤቱ አይገባም ነበር:: በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ንጉሥ በቤቱ ወንበሮች ላይ የተቀመጠው ዘኬዎስ በማጠሩ ምክንያት ነው:: የዘኬዎስ ነፍስ የዳነው በቁመቱ ማጠር ነበር:: እግዚአብሔር የመዳኑን ቀን የቆረጠለት ቁመቱን ሲያሳንሰው ነበር:: በምድር በመጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ በሕይወት መዝገብ ስሙ የተጻፈው ዘኬዎስ አጭር በመሆኑ ነው::

ስለ ቁመት የማወራ እንዳይመስልህ:: እግዚአብሔር ለነፍሳችን መዳን የሚያሳጥርብን ብዙ ነገር አለ::
እንደ ዘኬዎስ ቁመትህ አጭር ባይሆን የሚያጥርህ ነገር ግን አይጠፋም::

ይሄ ጎደለኝ የምትለው ከሰዎች አነስኩበት የምትለው ነገር አንዳች ነገር የለም? እሱን ማለቴ ነው::
ይሄ ይጎድለኛል ከሰው አንሳለሁ እያልክ አትማረር::
እጥረትህ መክበሪያህ ነው:: ጉድለትህም መዳኛህ ነው::

እግዚአብሔር ያጎደለብህ የመሰለህ ነገር ወደ ዛፍ እንድትወጣ ምክንያትህ ይሁን:: በጉድለትህ እንደ ዘኬዎስ ከፍ በልበት:: ያኔ ሰዎች አንተን አንጋጠው ከማየት ውጪ አማራጭ አይኖራቸውም::
ፈጣሪ በፍቅሩ ይይህ እንጂ ሰዎች ወዳንተ ያዘነብላሉ::  በቤትህ መዳን ይሆንልሃል:: ከዚያም ስላጠረህ ስለጎደለህ ነገር ፈጣሪህን ስታመሰግነው ትኖራለህ::

እመነኝ አንዳንድ ጉድለቶች እድሎች ናቸው::
ዘኬዎስ አጭር ባይሆን ይሄኔ በሾላው ዛፍ ጥርሱን እየፋቀ ይቀር ነበር::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
@gasha_tube