Get Mystery Box with random crypto!

ለትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት የሶስተኛ ወገን የትግበራ ስምምነት ተፈረመ   የኢት | ጋሻ ƬƲƁЄ ꍟ꓄ꃅꀤꂦᖘꀤꍏ

ለትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት የሶስተኛ ወገን የትግበራ ስምምነት ተፈረመ

 
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ለሚካሄደው የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክቶች አገልግሎት ቢሮ ጋር የሶስተኛ ወገን የትግበራ ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና የተመድ የፕሮጀክቶች አገልግሎት ቢሮ ተወካይ ወርቅነሽ መኮንን ተፈራርመውታል።ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በጦርነት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት በሚል ዕቅድ የመንግስት ብሄራዊ ማገገሚያ ፕሮግራም አካል ሲሆን ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተመድ የፕሮጀክቶች አገልግሎት ቢሮ አማካኝነት የሚተገበር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ይህ ፕሮጀክት በግጭት ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የመሠረታዊ አገልግሎቶችን እና ለአየር ፀባይ ለውጥ የማይበገር የማኅበረሰብ መሠረተ ልማትን መልሶ መገንባት እና የማሻሻል ውጥን ያለው ነው።ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ እና የፆታ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የባለብዙ ዘርፍ ምላሽ አገልግሎቶት ተደራሽነትን የማሻሻል ግብን የያዘ ነው።

በስምምነቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክቶች አገልግሎት ቢሮ በትግራይ ክልል የመልሶ መገንባት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማሻሻል እና የአየር ንብረት መቋቋም የሚችል ማኅበረሰባዊ መሠረተ ልማት የመገንባት ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል።በተጨማሪም ማኅበራዊ ተቋማትን በመደገፍ እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመምከር ማኅበረሰቡ ለሚፈልጋቸው አገልግሎቶች ፈጣን ምላሽ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው የተባለው።

በግጭት ምክንያት የተጎዱ መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማቶች መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ መስራትም ቢሮው ከመንግስት ጋር የገባው ስምምነት አካል መሆኑ ተገልጿል።ቢሮው በትግራይ ክልል አሁን ያለው ሁኔታ እስከሚስተካከል እና መንግሥት በክልሉ መደበኛ አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምር ድረስ ብቻ ቆይታ ይኖረዋል ተብሏል።


@gasha_tube