Get Mystery Box with random crypto!

ጌታ ከገጠመኜ ያስተማረኝን ላካፍላችሁ........ የምኖርበት ሰፈር ያው እንደማንኛችንም አካባቢ | Gaius Ministry

ጌታ ከገጠመኜ ያስተማረኝን ላካፍላችሁ........

የምኖርበት ሰፈር ያው እንደማንኛችንም አካባቢ ከፍተኛ የውሃ ችግር አለ። እና ጭራሽ ሰሞኑን ወር አልፏታል ውሃ ከመጣች።( ውሃን ያያችሁ ....... ያው መልሳችሁን አውቀዋለሁ " አላየንም !" ነው።)

ታድያ አማራጭ ስላጣን 2 ባለ 20 ሊትር ጀሪካኖችን ገዝተን በየቀኑም ይሁን እልፍ እያልን እንደአጠቃቀማችን ውሃ ይዘን መግባት የሰርክ ተግባራችን ሆኗል እኔና ሚስቴ።

ታድያ መኖርያችን 4ኛ ፎቅ በመሆኑ የህንጻው ጥበቃ በሸክም ይረዳናል። በቃ ደግሞ ሸሪካችን ስለሆነ ገና ብቅ ስንል እኔንም ባለቤቴንም ጠጋ ብሎ " ውሃ አመጣችሁ እንዴ?" ይልና ሁለቱንም አፈራርቆ በፈገግታ በታጀበ አገልግሎት 4ኛ ፎቅ ያደርስልናል። የኛ ድርሻ አንዱን አድርሶ እስኪመጣ ሌላኛው ጋር መጠበቅ ነው። በቃ ይህ ከወር ያለፈ ግንኙነት ነው....... ወዳጅ ሆነናል.... ተግባብተናል.... አንዳንድ ነገር ልናግዘው እንሞክራለን..... ውሃ ሲያደርስ ደግሞ የኪስ ነገር ጣል እናረግለታለን። ተገቢ ብለን ምናስበውንም አንዳንዴም ያቅማችንን ከፍ ልናረግለት እንሞክራለን።

ታድያ ትናንት ወድያ ምሽት እኔ ነበርኩ ውሃ ይዤ የመጣሁት...... እና ጥበቃው ወዳጄ ዳርጌ (ስሙ ነው) እንደወትሮው ጠጋ አላለኝም። ባይኔ ብፈልገውም አጣሁት። ለካ ህንጻው ጥግ ነገር ላይ ብርድልብሱን ተከናንቦ ተኝቷል። አሳዘነኝ! ትንሽ ብርድም ካፍያም ነገር ነበር። ጠራሁት እና ውሃ ማምጣቴን ነግሬ እንዲያደርስልኝ ጠየኩት። ገና ዞር እንዳልኩ ምስኪን ዳርጌ " እሺ" ብሎ ምንም ሳያቅማማ አንዷን ጀሪካን ወደ ትካሻው ከፍ ነገር አድርጎ እንደ ወትሮው ለመሸከም ሲል አምልጦት ኖሯል። ብቻ የሆነ ነገር " ደፍ ፣ ዧ" ሲል ድንግጥ ብዬ ስዞር ክው ብሎ ለማንሳት ይንተፈተፋል። ቲቪ የጣለ ነው ሚመስለው........ ለማገዝ ጠጋ ብዬ ሳይ የሆኑ ቦታዎች ጀሪካኑ ጨርመት ብሏል። በስጨት እንደማለት ቃጣኝ.... በውስጤ " ቀስ አይልም እንዴ?! ምን እዚህ....." አይነት ተሰምቶኛል። ጀሪካኑን ልገዛ ስል ዋጋው አስገርሞን ከሚስቴ ጋር በስልክ የነበረን ንግግር እና ግርምት ትዝ አለኝ። ዳርጌ አበሳጨኝ!!! ብቻ ዋጥ ነገር አድርጌ አይዞህ ምናምን ብዬ አሸካከምኩት እና አንዷን እንዲያደርስ ልኬ ሌላውን ይዤ መጠበቅ ያዝኩ።

ከዛ ያው ጌታ ከክስተቶች ብዙ ያስተምረኛል እላችሁ የለ?!....... መዓት ሃሳብ ይዥጎደጎድ ያዘ!

ሲጀምር ፕላስቲክ ጀሪካን ነው...... ተሰባሪ አይደል?! ሲቀጥል ቢበላሽ እንኳ ያን ያህል እኔን የሚጎዳኝ አይደለ.... ደግሞ ዳርጌ ስንት ግዜ ነው ያገዘኝ! ፈገግ እያለ! አንዳንዴ ክፍያ ጭራሽ አልቀበልም እያለ! ቢከብደኝ አደል እንዴ የእርሱ እርዳታ ያስፈለገኝ?!

መልስ ብዬ ማሰላሰል ያዝኩ ...... ጌታን አሰብኩት!

ስንት ግዜ ነው ስከሰክስ የታገሰኝ!!!! ያውም ጀሪካን ያልሆነ! ገና ከመነሻው እንደማንም የሰው ልጅ በጨለማ ስልጣን የነበርኩትን በልጁ ደም አጥቦ ቀድሶ ልጁ ያረገኝ። እንደ እኔ ያለውን ታማኝ አድርጎ ቆጥሩ አገልጋዩ ያረገኝ። ከዛም በኃላ በብዙ መውጣት መውረድ ፣ ከፍታ ዝቅታ፣ መውደቅ መነሳት የታገሰኝ!!!!!!!!!!!!!!!

ከስንት ወጥመድ የታደገኝ!

እንደገና እድል እየሰጠ እዚህ ያደረሰኝ!!!!!!!!!

ደሞ እኮ እርሱ እንደኔ ጥበቃውን እንደፈለኩት አቅም አጥቶ አጋዥ አስፈልጎት አይደለም።

ፍቅሩ እንጂ!!!!! ምህረቱ እንጂ!!!!! ጸጋው እንጂ!!! እሺታው እንጂ!!!!!

ጭራሽ እርሱ እኮ እንደኔ የኪስ ሳንቲም ሳይሆን ህይወት ቀድሞ የሰጠኝ ነው:: በእርግጥ ኑሮዬም በእርሱ ነው።

ኦው ይኽ ሁሉ ያሰብኩት ዳርጌ ከ4ኛ ፋቅ እስኪወርድ ነው። ግን በእንባ ታጠብኩ!

ሁለተኛውን ጀሪካን ፈገግ ብዬ አሸከምኩት.......

እሺ እንግዲህ ወዳጆች ምን ትላላችሁ!!!!!!

በሉ ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ልሰነዳዳ.....መልካም እሁድ!!!