Get Mystery Box with random crypto!

Fresenbet G.Y Adhanom

የቴሌግራም ቻናል አርማ fresenbett — Fresenbet G.Y Adhanom F
የቴሌግራም ቻናል አርማ fresenbett — Fresenbet G.Y Adhanom
የሰርጥ አድራሻ: @fresenbett
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 6.77K

Ratings & Reviews

2.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

1

3 stars

0

2 stars

1

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2023-06-10 15:25:03
ተቋማቶቻችንን ይደግፉ!

የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ለኦርቶዶክሳዊያን እጅግ ወሳኝ ነው:: ከኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ጋር ተደማጭነት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት አብረው ይመጣሉ:: ይህንን ለማምጣት ግን ሥራ ይፈልጋል!

ለመሆኑ ኦርቶዶክሳዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ተቋማትን ከፍ ለማድረግ ምን አስተዋጽኦ አበርክተዋል?

አስተዋጽኦ ማድረግን ከዚህ ይጀምሩ:: አሐዱ ባንክ 1 ሚሊዮን ደምበኞች ለመሙላት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: የባንክ ሒሳብ በመክፈት እንቀላቀል:: አክስዮን በመግዛት ባለቤት እንሁን:: ሒሳባችንን በማንቀሳቀስ ባንኩን እናግዝ::

#አሐዱ_ባንክ #1_ሚልዮን_ደንበኛ
1.3K viewsFre, edited  12:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-29 09:44:13 +• ዲያቴሪዎ •+

ክርስቶስ መሢሁ እንደሆነ መናገር በሚያሰድድበት እና በሚያስገድልበት፥ የጣዖት አምልኮም የሥነ-ምግባርና የሞራል ዝቅጠት እንዲስፋፋ ምክንያት በሆነበት በጥንቱ ዘመን ክርስቲያኖች በስውር እየተገናኙ የአምልኮ ሥርዓታቸውን ይፈጽሙ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። በተለይም በጥንቷ ሮም ውስጥ ነገሮችን በምሥጢር ሸሽጎ የመያዝ ብልሃት የሞትና የሕይወት ጉዳይ ስለነበር፥ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለሌላ ክርስቲያን የሚገልጡበት እና በምስጢር ተገናኝተው አምልኮ የሚፈጽሙበትን ቦታ የሚጠቁሙበት አንድ ዘዴ ነበራቸው።

በመንገድ የሚሄዱ ሰዎች ሲገናኙ አንዱ ክርስቲያን ከሆነ ዝቅ ብሎ በመሬቱ ላይ የክብ ግማሽ ይሥላል። ሌላኛው ሰው ዝቅ ብሎ ተመሳሳዩን አይነት ቅርጽ ጨምሮ የዓሳ ምሥል ከሠራ ሁለቱም ክርስቲያን እንደሆኑ ያውቁና በደስታ ሰላምታ ይሰጣጡ ነበር። ይህ ጥንታዊ የዓሳ ምልክት ኢኽቱስ (ግሪክ፡ ἰχθῡ́ς) ሲባል፥ ጌታችን ኅብስትና ዓሳ አበርክቶ ማብላቱን አብነት ያደረገ ምልክት ነው። ይህ ምልክት ከሁለተኛ መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በክርስቲያኖች ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ማስረጃ ያለ ሲሆን፥ በተለይ ደግሞ የሮም መንግሥት ከፍተኛ ስደትና መከራን በክርስቲያኖች ላይ በሚያደርስበት ጊዜ ክርስቲያኖች በምስጢር የሚገናኙበትን ቦታ ለመጠቆም የዓሣ ምልክቱን ይሥሉ ነበር። ይህንን የሚያውቅ አንድ ክርስቲያንም የተሣሉትን የዓሣ ምልክቶች እየተከተለ ወደ ምሥጢራዊው የአምልኮ ስፍራ ይደርስ ነበር።

በሐዲስ ኪዳን ስንመለከት፥ አንድም ታላቁ ቅዱስ ዮሴፍ፥ አንድም ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለምስጢራዊነት አብነት ሆነው ተገልጠው እናገኛለን። ቅዱስ ዮሴፍ ለእመቤታችን ጠባቂ ሆኖ ሳለ ጸንሳ መገኘቷ እጅግ አሳዝኖት ነበር። በሕገ-ኦሪት መሠረትም ለካህናቱ ሊነግር እና ሊያስፈርድባት ይችል ነበር። እርሱ ግን የእርሷን ነገር በአደባባይ ላይዘራ፥ ለካህናቱ ፍርድም ላያጋልጣት "ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።" (ማቴዎስ 1:19) በዚህም በልቡ ነገሩን ይዞ ቶሎ መፍረድና ለውሳኔ መቸኮል እንደማይገባ አብነት ሆነን፤ በኋላም የእግዚአብሔር መልአክ በሕልሙ ተገልጦ የእመቤታችንን መጸነስ ምስጢር አስረድቶታል። እመቤታችንም ደግሞ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ከወለደች በኋላ ልጇ የሚያደርገውን እያየች፥ የሚናገረውንም እየሠማች ብትኖርም ሁሉን አውጥታ በአደባባይ አልተናገረችም፥ ያደረገችውንም የሚገልጸው ቅዱስ ሉቃስ "እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልቧ ትጠብቀው ነበር።" (ሉቃ 2:51) በማለት ይነግረናል። መጠበቋን የሚገልጸውን ቃል ግዕዙ ተዐቅብ ሲለው፥ ግሪኩ ዲያቴሪዎ (ግሪክ፡ διατηρέω) ይለዋል - ከመጠበቅም ባሻገር "በሚገባ እያስተዋሉ መመርመር" የሚል ትርጉምም አለው።

የቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ ሆኖ ነገርን በልብ መያዝ፥ የእመቤታችን ምስጢር መጠበቅ እና የቀደምት ክርስቲያኖች ብልሃት ለእኛ ምን መልእክት አለው?" የሚለው ጥያቄ ዛሬ ላለንበት የታሪክ ወቅት እጅግ ወሳኝ ነው። ዛሬ ላይ ኦርቶዶክሳዊያን የዝምታ ጥቅም ተዘንግቶን፥ ነገሮችን በአስተውሎት መመርመርና በልብ ነገሮችን መጠበቅም ተስኖን የውጭም የውስጥም ጉዳያችንን በአደባባይ ስናሰጣ እና ስናራግብ በሰፊው እንታያለን። ይህ አካሄድ የቅዱስ ዮሴፍን ጻድቅነት ለሚናገር፥ የእመቤታችንን እናትነት ለሚያምን፥ የቀደምት ክርስቲያኖችንም ፈር ለሚከተል ኦርቶዶክሳዊ ያልተገባ አካሄድ ነው።

በዘመናችን ከተዘነጉ ትሩፋቶች መካከል ዝምታ አንዱ ነው። ፒርኬ አቮት በተሰኘና የአይሁድ ሊቃውንት በግብረገባዊ ጉዳዮች ላይ ያስተማሯቸውን ትምህርቶች ሰብስቦ በያዘ መጽሐፍ ላይ የገማልያል ልጅ የሆኑት ስምዖን ቤን ገማልያል፦ "ሕይወቴን ሙሉ በጠቢባን መካከል አድጌያለሁ፥ ለሰው ልጅ ግን ከዝምታ የተሻለ አንዳች ነገር አለመኖሩን፥ ከመማር ይልቅ ማድረግ [በድርጊት መግለጥ] የተሻለ መሆኑን እና ንግግር የሚያበዛ ኃጢአትንም እንደሚያበዛ ተረድቻለሁ።" ይሉናል። ዝምታ ስንል በሆነው ባልሆነው እንዲሁ ከማውራት መቆጠብን ይጠቁማል፤ ከማውራት ይልቅ መሥራት ላይም ያተኩራል። ብጹእ አቡነ አንጌሎስም "ዝምታ ማለት የምንናገረው አጥተናል ማለት አይደለም፤ እግዚአብሔር ለመናገር ተገቢውን ጊዜ እስኪሰጠን ድረስ አንደበታችንን ሰብስበናል ማለት እንጂ።" የሚሉትንም ማስታወስ ይበጃል።

ሁሉን በሁሉ ቦታ ባለማውራት፥ በማናውቀው ጉዳይ ባለመጻፍና ባለመናገር፥ ከእርሱ ይልቅ ማድረግ በምንችለውና በተፈቀደልን ላይ በማተኮር ከቤተክርስቲያን ጎን እንቁም።

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን!

Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
3.5K viewsFre, edited  06:44
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-29 09:34:31
2.3K viewsFre, 06:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-28 12:15:16 +• ከንቱ ቃላቶች •+

አንድ ቆየት ያለ “A Thousand Words” (አንድ ሺህ ቃላት) የሚል ታዋቂው ተዋናይ ኤዲ መሪፊ የሚሰራበት ፊልም አለ። ፊልሙ አንድ ስኬትን ለማግኘት ማንኛውንም አይነት ውሸት ለመዋሸት ዝግጁ የሆነን ሰው ታሪክ ያስቃኘናል። በአንድ አጋጣሚ ከዚህ ሰው ቤት ጀርባ አንድ ዛፍ ይበቅላል። ሰውየው አንድ ቃል በተናገረ ቁጥር፤ ከዛፉ ላይ አንድ ቅጠል ይረግፋል። ቅጠሎቹ ረግፈው ሲጨርሱም እንደሚሞት ይነገረዋል። ይህ ሁኔታ ለቃላቱ እጅግ እንዲጠነቀቅ ሲያደርገው እና ከሰዎች ጋር ያለውን ተግባቦት እጅግ አስቸጋሪ ሲያደርግበት ፊልሙ ያስቃኛል።

ለመሆኑ በየቀኑ እንደልብ ቃላቶቻችንን ለምንጠቀም፤ ጥቅም ያለውንም ሆነ የሌለውን ነገር በአንድ ላይ ስንናገር ለምንውል፣ ባስ ሲልም ሰዎችን በመስደብ እና በመዝለፍ ቃላቶቻችንን ለምናባክን ሁሉ በፊልሙ እንዳለው ገጸ ባሕርይ የተወሰኑ ቃላት ብቻ እንደቀሩን፤ እነዚህም ቃላት ስንጨርስ እንደምንሞት ቢነገረን ምን እናደርግ ይሆን? ዝምታን እንመርጥ ይሆን? እንዲሁ የመጣልንን ተናግረን እና ቃላቶቻችንን ጨርሰን እንሞት ይሆን? የምንጠላውን ሰው እንረግምበት ይሆን? ቃላቶቻችንን ለምን እንጠቀምባቸው ይሆን?

ቃላት እንደ ቢላዋ ናቸው። ቢላዋ በቀማኛ ወይም በሽፍታ እጅ ሲገባ ነፍስ ያጠፋል። ቢላዋ በሐኪም እጅ ሲሆን ደግሞ የታመመ አካልን ቀድዶ ያድናል። ቃላትም እንዲህ ናቸው። ቃላት ያቆስላሉ። ቃላት ያድናሉ። ቃል መዘዝ እንዳለው የተረዳው ማኅበረሰባችንም “የቃል ወለምታ በቂቤ አይታሽም” ብሎ ተርቷል። ለመሆኑ “አንተ ሰነፍ ነህ!”፣ “አንቺ አትችይም!”፣ “አንተ ዋጋ የለህም!”፣ “አንቺ አትረቢም!” በሚሉ ቃላት ስንቱ ልቡ ተሰብሮ ይሆን? የስንቱ የስኬት መንገድስ ተጨናግፎ ይሆን? እኛስ ብንሆን፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንዲህ ያሉ ቃላትን ተናግረን ያሰናከልነው ሰው ይኖር ይሆን?

በእግዚአብሔር መንፈስ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉልን ቅዱሳን ሰዎች ስለ ቃል ኃይል ተረድተው ብዙ ጥበብን አጋርተውናል። ታላቁ ቅዱስ ጳውሎስም እንደ ክርስቲያን ሊኖረን የሚገባንን የቃላት አጠቃቀም ሲገልጽ እንዲህ ይለናል፦

“ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።” (ኤፌሶን 4፡29-31)

ቅዱስ ጳውሎስ በተናገረው ቃል ውስጥ ክፉ ቃል ከአንደበታችን መውጣት አንደሌለበት፣ ክፉ ቃላትን መናገር የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን እንደሆነ፣ በንዴት መናገር፥ መቆጣት፥ መጮኽ፥ መሳደብ ሁሉ ክፋት እንደሆነ እና የክርስቲያኖች መገለጫ ሊሆን እንደማይገባ ይነግረናል። ይህንን ከነባራዊው ሕይወታችን ጋር እናነጻጽረው። በቅርብ ባሉ ወዳጆቻችን ዘንድ የምንታወቀው ቁጡ በመሆናችን ነው? ሰው ስለጩኸታችን አቤቱታ ያቀርባል? “ተናድጄ ነው” ወይም “ተቆጥቼ ነው” በሚል ሰበብ ሌሎችን አንሳደባለን? ይህ ከሆነ በየቀኑ መንፈስ ቅዱስን እያሳዘንን እንደሆነ ልንረዳ እና በንስሃ ወደ እግዚአብሔር ልንመለስ ይገባል። ከዚህ ባለፈም እነዚህ ቃላቶቻችን እንደሚያስፈርዱበት መረዳት አለብን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና፥ ከቃልህም የተነሣ ትኮነናለህ።” (ማቴዎስ 12፡36-37) በማለት አስጠንቅቆናል።

ታዲያ፤ የእውነት በከንቱ ለምንናገራቸው ቃላት ሁሉ በፍርድ ቀን ከክርስቶስ ፊት መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነን?

Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
1.1K viewsFre, edited  09:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-28 12:15:09
858 viewsFre, 09:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-27 08:35:38 +• 20 ወንድማዊ ምክሮች •+

1. ፈገግታ ጌጥ ነውና ከፊትህ ላይ አይለይህ::

2. ብዙ ማውራት ሰውን ያታክታልና በንግግርህ ቁጥብ ሁን::

3. የምትጀምራቸውን ነገሮች ሁሉ በጸሎት ጀምር::

4. ያልተገባ ነገር ተናግረህ ትዝብት ላይ እንዳትወድቅ የማታውቀውን ነገር አላውቅም ለማለት አትፈር::

5. በሁሉ ነገር ላይ አስተያየት ካልሰጠሁ አትበል::

6. በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን "እግዚአብሔር ይመስገን" ማለትን አትርሳ::

7. በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምጽዋትን የምትሰጥ ሁን::

8. ለመቀየም የዘገየህ ይቅር ለማለት የፈጠንክ ሁን::

9. ሕይወትህን በእቅድ ምራ::

10. በጥበብ ማደግ ገደብ የለውምና ትምህርትን በቃኝ አትበል፤ ሊያስተምርህም ፈቃደኛ ከሆነ ሰው ሁሉ ተማር::

11. ውሳኔን ለመስጠት ችኩል አትሁን::

12. በሰው እንዳትናቅ የዋህ ሁን እንጂ ጅል አትሁን:: ሰዎች እንዳይርቁህ ብልጥ ሁን እንጂ ተንኮለኛ አትሁን::

13. በሰዎች ፊት ያለ ፍርሃት እንድትቆም የምትማራቸውን ነገሮች አጥርተህ ተማር::

14. ክርስትና ሕይወት ነውና፤ የምታምነውን በሕይወትህ ለመተግበር የተጋህ ሁን::

15. የሚያስቀይምህን ነገር ልትሠማ ትችላለህና ሰዎች የሚያወሩትን በድብቅ አትስማ::

16. በአመጋገብህ ትዝብት ላይ እንዳትወድቅ ስትመገብ አትስገብገብ::

17. አዳማጭ ከማጣት የቆሰሉ ብዙ ሰዎች አሉና፤ ሰዎች ችግራቸውን ሲያዋዩህ ጆሮ ስጣቸው::

18. ምጽዋት ለጠየቀህ መስጠት ስንኳ ባትችል "እግዚአብሔር ይስጥልኝ" ማለትን አትርሳ::

19. በእንስሳት ላይ ጨካኝ አትሁን::

20. የሰዎችን ሁኔታ የበለጠ ለመረዳት "እኔ በእነርሱ ቦታ ብሆን ምን አደርግ ነበር?" ብለህ ራስህን ጠይቀው::

Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
2.6K viewsFre, edited  05:35
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-27 08:35:05
903 viewsFre, 05:35
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-25 12:06:09 +• የምታሰላስለው ምንድር ነው? +•

ድንቅ የሆነውን የሰው ልጅ አእምሮ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንደሚነግሩን ከሆነ፤ የሰው ልጅ በቀን ውስጥ በአማካኝ ከስድስት ሺህ እስከ ሰባ ሺህ የሚደርሱ አሳቦችን ያስባል። ይህ እጅግ ብዙ አሳብ ነው! እንግዲህ ይህ ቁጥር የመጣው ጊዜ ሰጥተን የምንቆዝምበትም፤ ለአፍታ ውልብ ብሎ የሚጠፋውም አንድ ላይ ተቆጥሮ ነው። እነዚህን ሁሉ አሳቦች ማስታወስ አዳጋች ቢሆንም፤ ቢያንስ ግን በየቀኑ ልባችንን ሰጥተን የምናስባቸው አሳቦች ግን ከትውስታም አልፈው ማንነታችንን የሚቀርጹ በመሆናቸው የሚረሱ አይደሉም። ለዚህም ይመስላል “አንተ ማለት የምታስበውን ነህ” (You are what you think) የሚለው አባባል በብዙዎች ተዘውትሮ የሚጠቀሰው። እኛ ደግሞ አቃንተን “አንተ ማለት የምታሰላስለውን ነህ” (You are what you meditate upon) ብንለው ይበልጥ ይሰምራል።

ክርስቲያን ምን ሊመኝ ይገባል? አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ ሊመኛቸው እና ሊናፍቃቸው ከሚገቡ ነገሮች ዋነኛው ቅዱስ መሆንን ነው። ቅድስና ውበት ነው። ቅድስና እግዚአብሔርን መምሰል ነው። በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን የተስተጋባው “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌዋውያን 11፡44፤ 1 ጴጥሮስ 1፡15) የሚለው የእግዚአብሔር ትእዛዝ ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁሌም መረሳት የሌለበት መመሪያችን ሊሆን ይገባዋል። ሁላችንም ወደዚህ ቅድስና መሄድ ካለብን ታዲያ፤ “ይህ ቅድስና እንዴት ይገኛል?” የሚለውን ጥያቄ መመርመር ያስፈልጋል። ለዚህ ጥያቄያችን መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ምላሽን ሲሰጠን፤ “የተባረከ ሰው” ወይም “ብጹዕ ሰው” የምንለውን አይነት ሰው ላይ የሚታዩ መገለጫዎችን ያጋራናል። እነዚህ መገለጫዎች አሉታዊ (የተባረከ ሰው የማያደርጋቸው) እና አዎንታዊ (የተባረከ ሰው የሚያደርጋቸው) ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን። ከእነዚህም መካከል ጻድቅ ሰው ሊያደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችን ሲዘረዝር “በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።” (መዝሙር 1፡2) ይላል።

እነዚህ “በእግዚአብሔር ሕግ መደሰት” እና “የእግዚአብሔርን ሕግ ቀን እና ሌሊት ማሰብ” የሚሉት ሁለቱ መርሆዎች ጻድቃንን ሁሉ አንድ የሚያደርጉ ናቸው። በእግዚአብሔር ሕግ ሳይደሰቱ ቅዱስ መሆን፤ ሕጉንና ቀንና ሌሊት ሳያሰላስሉ እና ሳይተገብሩ ብጹዕ መሆን አይታሰብም። የተባረከ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ሕግ ታላቅ ቦታ አለው። ቅዱሳት መጻሕፍትን ጊዜ ሰጥቶ ይመለከታል፤ ያነበበውን ቃል ጊዜ ሰጥቶ ያሰላስላል፤ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ጠንቅቆ ይረዳል፣ በሕይወቱም እንዴት አድርጎ መተግበር እንዳለበት ያስባል። ሕይወታችን እንዲህ ሲሆን የእግዚአብሔርን ቃል ጣዕም እንረዳዋለን። ነቢዩ ኤርሚያስ “ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ” (ኤርምያስ 15፡16) በማለት ይገልጽ የነበረው ይህ ጣዕም ገብቶት ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ላይ ስለ እግዚአብሔር ቃል ሲናገር “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” (ቆላስይስ 3፡16) በማለት ያዝዘናል። እኛ ግን የእግዚአብሔር ቃል በሙላት አለብን? እንዲያው ሙላቱ ቀርቶ በጥቂት ስንኳ የእግዚአብሔር ቃል በእኛ ውስጥ አለ? በቀን ውስጥ በጸሎት መንፈስ ሆነን የእግዚአብሔርን ቃል ለመመርመር፤ ስለ እግዚአብሔርም ለማሰብ ምን ያህል ሰዓት ወይም ደቂቃዎችን እንሰጣለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስናገኝላቸው፤ እኛም አብረን ከነቢዩ ኤርምያስ ጋር “ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ” ማለት ያልቻልንበት ምክንያት ይገለጽልናል።

በቀንም ሆነ በሌሊት የምናሰላስላቸው ነገሮች ቀስ በቀስ ማንነታችንን ይቀርጻሉ። በመሆኑም አሳቦቻችንን በጥንቃቄ መፈተሽ አለብን። እናስ ወንድሜ፤ የምታሰላስለው ምንድር ነው? አንቺስ እህቴ፤ ቀን እና ሌሊት በአእምሮሽ የሚመላለሰው ምንድር ነው?

Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
1.2K viewsFre, edited  09:06
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-25 12:04:31
948 viewsFre, 09:04
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-09 08:11:10

541 viewsFre, 05:11
ክፈት / አስተያየት ይስጡ