Get Mystery Box with random crypto!

#ምርጥ ( #ምርትነሽ_የማነ) እቴትዬና..... እሜ አደዬና ......ሀርሜ በየ ፈርጀ ..... | ፍቅር እና ጠበሳ

#ምርጥ ( #ምርትነሽ_የማነ)

እቴትዬና..... እሜ
አደዬና ......ሀርሜ
በየ ፈርጀ ........ፈርጁ
በእያንዳንዱ ቋንቋ ፥ ቃላት ቢወዳጁ
አንቺን .....እኮ እናቴ
የጠዋት አስኳላ ፥ የልጅነት ሀብቴ
ኑር አንተ ለኔ .......ባይ
ቅንጣት ሳይታወስ ፥ ላንቺ ያንቺው ጉዳይ
በጉያሽ አቅፈሺኝ ፥ በጪንጫ ተኝተሽ
ውሀ ባፍሽ ርቆ ፥ ወተቱን ያጠጣሽ
ማጀት ያጠቆረሽ
ረሀብ ያከሳሽ
ጎኔን ....... ጨርቄን...... ማቄን
የሚሉት ጥበቃ ፥ ከራስ በላይ ንፋስ ፥ ሰይሞ መዳከር
ላንዲት ነብስ ስስት
ላንድ አካል መንቧቸር
ከራስ በላይ ልጄ'ን
በሚል ልግስና ፥ እድሜን በመቸርቸር
ብ 'ርክ በማለት ፥ ብርክሽን የረሳሽ
በመከነ ቀለም ፥ ብዕርሽ የጠፋች።
ያ..............#ፀሀይ ውበትሽ
ኩሽና ተሳስሮ ፥ ከምጅጃ ግርጌ፥ ዕድያው የቀረ
ወዘናሽ ተሟጦ ፥ ገፅሽ የጠቆረ
በመጨናበስ #ነው
አካልሽ ለጋሱ ፥ አይነ ግቡ መልኬን ፥ ዛሬ የወቀረ ።

የአፍላነት ግዜሽ
ጥንቡሳሱን ጥሎ ፥ ያለ እድሜሽ ያረጀሽ
ደ 'ስታን ልክ እንደ መርዝ
ለልጅ በመኖር ውስጥ ፥ ዘመንሽ የቀማሽ
በአለሙ መሀል ፥ ለአለም እንግዳ
ትክሻሽ የሳሳ ፥ ቅስምሽ የተጎዳ
የህይወት ቀንበር ተጫኝ
ለፍሠሀ ባዳ !!
ሀኪም እናታለም
#ኮስማናዋ #እናቴ!!!
የህይወት መቅድሜ
የጉም ቀን መብራቴ
ተስፋ አለምሽ ይጥና
#በርቺልኝ በሞቴ
እናትነትሽ ነው ፥ በዚህ ልፋጭ አለም ፥ የቀን ክራሞቴ።

የሰማዩ ንጉስ የምድሩም ጌታ
ከምንም አብልጦ ፥ እናቱን ይወዳል
ትንሽም ሲራሩ
እናቴ ያሉ እንደው ፥ ምዕንተ ማርያም ፀሎት ይማለዳል
ውህብቶ ብዙ ነው ፥ ዳና በመከተል ፥ በገፍ ይሰደዳል
እናቴ ለሚሉት እናት መሆን ያውቃል
ስለዚህ ....
ልጄን ብለሽ አንቺ ፥ ፊቱን እንደ ሰማሽ
ያብቃኝ ....
አንቺም ያብቃሽ....
ለልጅ የተሰዋ
አድሮ የበረታ ፥ የህላዌ ጥዋ
ብሩህ ጀምበር ገጥሞ
በልጅ የፈዘዘ ፥ ዳግም በልጅ ቀልሞ
እንጥፍጥፍ አለም ....በእድሜ ስልቻ ፥ ጠብቆ ተቀምቅሞ
እያጠነጠነ...... የግዜ ሰሌዳ ፥ በመቁጠሪያ ሲታሽ
አድማስ ተሻጋሪ ... #ቦግ!!! ብሎ ማታሽ

ውድ ሸማሽ ሆኜ ፥ መቀነት ያውለኝ
ለውበት ...ለድጋፍ ፥ መጠቅለል የቀናኝ
ገንዘብ ....መቋጠሪያ
ውጋት ......ማባረሪያ
ላዱኛ ቀን ብርታት
ለጭንቅ ቀን ፅናት
አድርጎ .....እኔን ላንቺ ፥ ፈቅዶልኝ ፈጥሪ
የእናቱን ቀን አውጪ ፥ በወዘናው ጣሪ
ግብ ቀንቶት ፅናቴ
ሹልክ ብለሽ ወጥተሽ ፥ ከኑሮ ግርግር
ከእንጉርጉሮ አለም ፥ ጠማማ ውንግርግር
ምርቃትሽ ደርሶኝ ....መነን ሁኚ እናቴ
ባንቺ ውስጥ እንደኖርኩ ፥ በኔ ትኖሪ ዘንድ ፥ ይባረክ ጉልበቴ።

#አብርሀም_ተክሉ ( #መርዕድ)

@fonkabcha1
@fonkabcha1