Get Mystery Box with random crypto!

​​​​​​​​​​​​​​​​​ ሴትን አላምንም የመጨረሻው ክፍል | ፍቅር እና ጠበሳ

​​​​​​​​​​​​​​​​​


ሴትን አላምንም

የመጨረሻው ክፍል


ፀሀፊ ሱለይማን መሀመድ



ሄሎ አለኝ የአህላምዬ የማይመስል ድምፅ

አህላም ነሽ?

አይደለሁም ሐያት ነኝ ሰዒድ ብላ መለሰችልኝ ፤ ድምፇ ይቆራረጣል አንዳች የመረበሽ ስሜት ያለው ይመስላል.....

ሀዘን ጥላውን ጥሎብኝ ብቸኝነት እንደ ብርድ ሰቅዞ የያዘኝ መሰለኝ ፤ የአህላም ድምፅ የለም  እህቷም የሀዘን ቀንዲሏን ልትነፋ በሚመስል ድምፅ መናገር እያቃታት አህላም ትንሽ አሟታል ፤ ከቻልክ ሆስፒታል ና ግን ብዙም አይደለም ህመሙ ፤ ማየት ከፈለግክ ብዬ ነው ብላ ያለችበትን ሆስፒታል በምልክት ነግራኝ ስልኩ ተዘጋ ፤ ከዚህ ቡኃላ መድረሻዬን እንጂ በምን መንገድ እየሄድኩኝ እንደሆነ አልገባኝም ግን አንድ ቦታ መድረስ ነበረብኝ።

መንገዴ ላይ ሁሉ መልኳና ያ ውብ ገፅታዋ የሰርግዋ ቀን የነበረው ፈገግታዋ ይታየኛል፤ እርሱን ሳስብ አቅምና ጉልበት እየሆነኝ ወደ ሆስፒታሉ ለመድረስ እጓጓለው።

በቀዩ ገላዋ ላይ ነጩን ቬሎ ለብሳ ፤ ነጫጭ ጉትቾችን በጆሮዎቿ ላይ አንጠልጥላ ፣ ያ ውብ በሆነው አንገቷ ላይ ሀብል አድርጋበት ፣ በሚያስደምም እግሮቿ ላይ ነጭ ጫማ ተጫምታ ከሰርጉ አዳራሽ ላይ ቁማ ያየሗት ሚስቴ ዛሬ ታማ ሀኪም ቤት ገብታለች ፤ ዛሬ እርሷን ማዳን ካልቻልኩኝ ምኑን ባል ሆንኩኝ ፣ ምኑን ብረት መዝጊያ ተባልኩኝ ፣ ዘላላም የአንቺው ነኝ ብዬ ቃል የገባሁላትስ ምኑ ጋር ነው?

ሆስፒታል ስደርስ በሰዎች ግርግር ተሞልቷል ፤ ዙሪያውን ሳጠና የአህላም ወንድምና እህት ሌሎች ብዙ ቤተሰቦቿ በትካዜ ቆመዋሉ ፤ እንባ እየተናነቀኝ  ሰውነቴ እያንቀጠቀጠኝ ቢሆንም ወደ ሐያት ጠጋ ብዬ።

አህላምስ? አልኳት

ውስጥ ገብታለች ዶክተሮች እያዯዋት ነው።

ምን ሆና ነው? እንባዬ እየፈሰሰ

እኔ እንጃ ሰሞኑ ልቤ እያለች ነበር የድካም ስሜት እየተሰማት ነበር ፤ ዛሬ ግን ተዝለፍልፋ ወደቀች በስልክ ስታወራህ ደህና ነኝ ስትልህ የነበረው እንዳትጨነቅ ነው ፤ መታመሟን ብናቅም ለአንተ መናገር እንደሌለብን አስጠንቅቃን ነበር ፤ ሰዒድ ከአንተ ጋር ከመጣች ቡኃላ ሁኔታዋ ልክ አይደለም ፤ እንቅልፍ አተኛም ፣ ታለቅሳለች ፣ ምግብ አትበላም ደግሞ መተንፈስም እየከበዳት ነበር ዛሬ ግን ደከመች ብላ አለቀሰች።

በደከመሽ ሰዓት ጥላሽ ኝ ብዬ ዛሬ ግን ጥላዋን ነጠቅኳት ፤ ጋሻሽ ነኝ ከችግሮችሽ ሁሉ የምከላከልልሽ ብዬ ቃል ገብቼ ዋሸሗት ፣ የደስታሽ ጊዜ ደስታሽን አድምቄ በችግርሽ ሰዓት ችግርሽን ተከፍዬ ከጐንሽ እቆማለው ብዬ ዛሬ ግን ብቻዋን ለእነዛ ህልምን በሳጥን ለሚያደርጉ ነጭ ለባሾች ሰጠሗት።

የአህላም ቤተሰብ? ሁለት ዶክተሮች ነበሩ

ሁሉም ተሰብስቦ ሄዶ "እኛን ነን"አያሉ

አንደኛው ዶክተር

አዝናለው! ህይወቷን መታደግ አልቻልንም ፤ አረፈዳቹ ፈጣሪ መፅናናቱን ይስጣቹ ብሎ ወደ መጣበት ተመለሰ።

የእኔ ናፍቆት ፣ የህይወቴ ማዕረግ ነፍሷ ከስጋዋ ተነጠለ ፤ የዘመናት ውጥኗ እና ያ መልካም ስብዕናዋ በጨረቅ ተሸፈነ ፤ ረጋ ባለ ድምፅ ጠርቼ አቤት የምትለኝ  አህላም ዛሬ ጮኼ ብጠራትም ጆሮ አልሰጥ አለችኝ።

ሁሉም ይጠሯታል የእኔ ልጅ ፣ የእኔ ከርታታ ፣ አባቷን  መሳይ ፣ እህቴ ፣ የእኔ እናት ፣ አበባዬ ፣ ለማን ጥለሽኝ ሄድሽ እያለ ያለቅሳል።

እኔስ ማን ብዬ ላልቅስ እናቴ ፣ እህቴ ፣ አባቴ፣ ጓደኛዬ ፣ ሚስቴ? ሁሉ ነገሬ እኮ ነች ፤ ሁሉ ነገሬን አጣሁኝ በመንገድ ላይ ተጠልፍኩኝ ፣ የበራው ሻማዬ ጠፋ ፣  ጐጆዬ ላይ ዳግም ትልቅ ጨለማ ተጋረደበት ፤ ደህና ነኝ ብላ እርሷ ግን የለችም ፤ አህላምዬን አጣሗት ፀ በስልኳ ውስጥ የሚሰማው የህመም ድምፅ በደህና ነኝ ቃል እየተሸፈነብኝ ፣ ለማሜ ምን ብዬ ልናገር? አደራዋን የበላሗት እናቴስ ነፍሷ እንዴት ያርፍ ይሆን?


አላውቅም መንገድ ላይ እየሄድኩኝ ነው ፤ ሰዎች እኔን አበደ ይሉኛል ግን ምንድን ነው ማበድ ፤ ቀኑ ምን እንደሆነ አለማወቅ ፣ የተቀደደ ልብስ መልበስ ፣ ጫት እጅ ላይ ይዞ መዞር ነው?

እኔ አላበድኩም ሁሉም ሰው መንገድ ላይ እያየ ይሸሸኛል አብጄ ነው እንዴ?

የአንዲትን ቆንጆ ሴት ፎቶ ይዞ ከተማ ላይ መዞር ፣ የሆነ ሆስፒታል ሂዶ ህልሜን መልሱልኝ ማለት እብደት ነው እንዴ?

እኔ አላበድኩም ፤ ምኑ ነው እብደት?

ስምሽን ሲጠሩ ማልቀስ ነው እብደት?
እንደ ጅል መሳቅ ነው እብደት?
ከሰካውት ሰንደል ጠረን መሳብ ነው እብደት? 
በጫት ገለባ መሬቱን መሞንጨሬ ነው እብደት?

እንድረሳት ያ ሁሉ መሆኔ ነው እብደት?

 
ለምን አትተውኝም? 

ልረሳትስ ብል መች እረሳታለው ፤ ሁሉ ቦታ እርሷ አለች ያልተራመድንበት  ያልተጓዝንበት መንገድ የት አለ?  ያልተቀመጥንበት ያለወራንበት ጐዳና መች ተዘረጋ?

ጐዳናው ላይ መቀመጥ ነው እብደት ፣ ማብድ ምን እንደሆነ አህላምዬ ታቀዋለች ፤  እርሷን አግኝታቹ ጠይቋት እኔ ግን አላበድኩም ፤ አቅሌ እርሷን እንጂ አያስብም ፤ ይህ ለኔ እብደት አይደለም። 

ግን ይህው እርሷን እየጠበቅኩኝ ፣ ስለእርሷ እየገጠምኩኝ አለሁኝ መግጠም ማበድ ነው?

ሻማው ሲጠፋ
~~~~
ሀዘን ካሰመጠው
ጨለማ ከዋጠው ፤
ከቀዝቃዛው ቤቴ አንድ ሻማ በርቷል
የፍቅራችን ዕድሜ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡

አንቺ ግን የለሽም
ሁሉ ሞልቶ ሳለ አንቺ ግን የለሽም ፤

እንደ ባለቅኔው ቃላት እንዳጠረው
ትመጪ እንደው እያልኩ ልክ እንደ ዜመኛው
ተስፋ ባጣ ሻማ እጠብቅሻለው፤
ቢሆንም አትመጪም
ግና ተስፋ አልቆርጥም ፡፡

እኚ ክፉ ሰዎች ክፉ ወዳጆቼ
ስጋዬ ያልኳቸው ክፉ ዘመዶቼ ፤
አትመጣም ይሉኛል ፥ ሞታለች ይሉኛል
"አብዷል" እያሉ አምተው ያሳሙኛል
ሄዳለችም ብለው ልቤን ያቆስሉኛል፡፡

እኔ ግን
ተስፋ ባጣ ሻማ እጠብቅሻለው
ቢሆንም አትመጪም
ይህንን አውቃለሁ
ግና ተስፋ አልቆርጥም
መቁረጥም አልችልም

ግና ፍቅሬ የት ነሽ ፥ የት ይሆን ያለሽው
ምን ባደርግሽ ይሆን እንዲ የጨከንሽው ፤
ላልተውሽ ላትረሽኝ በፍቅር የማልነው
ምንስ ባስቀይምሽ ቃሉን የረሳሽው፡፡

ጭር ካለው ቤቴ አንድ ሻማ በርቷል
የፍቅራችን እድሜ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡

ከአንድ አንቺ በስተቀር እዚህ ሁሉ ሞልቷል
የምንወደው ዜማ ቤት ውስጥ ያስተጋባል
የምትወጂው ምግብም ፥ ሽታው ልብ ያስርባል
የምወደው ሳህን ከፊቴ ተቀምጧል
አልጋውም ተነጥፏል
የፍቅራችን ምሽት በጨረቃ ደምቋል
ግና ፍቅሬ
አንቺ ብቻ ቀርተሽ ሁሉም ባዶ ሆኗል፡፡

ለፍቅራች ዕለት
ለዚህ ጣፋጭ ምሽት ያበራሁት ሻማ
'ላዩ ሲበራ ፥ ከታቹ የደማ ፤
ሚስጥር ይነግረኛል
እውነት ያሳየኛል፡፡

በመስኮት የገባ ንፋስ ሲያረብበት
ብርሀኑን ሊያጠፋ ገፍቶ ሲመጣበት ፤
እርሱ አጎንብሶ ፥ ንፋስ ያሳልፋል
ዕድሜ ለመቀጠል ዕድሜውን ይቀጥፋል ፤
ጭር ካለው ቤቴ ያበራሁት ሻማ
ሚስጥር ይነግረኛል
እውነት ያሳየኛል
"ፍቅርህስ ?" ይለኛል፡፡

ፍቅሬ ምን ልበለው
ቀርታለችም አልል ፥ መጥታለች አልለው
አንድ ሻማ ይዤ እጠብቅሻለው ፤
ቢሆንም አትመጪም
ይህንን አውቃለው ፤
ባውቅም ተስፋ አልቆርጥም
መቁረጥም አልችልም፡፡

ውዴ...
አንቺን ለመጠበቅ ያበራሁት ሻማ
'ላዩ ሲበራ ፥ ከታች 'እየደማ፡፡

አሁን ሻማው ጠፍቷል ፥ እኔ ግን ቆያለው
ለተስፋ ብርሃኔ ልቤን አነዳለው
ቀልጦ ያለቀ ዕለት እኔው እመጣለው፡፡