Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል.......8 (በእውነተኛ ታሪክ የተመሰረተ) አዘጋጅ፦ ፍቅርን በቃላት . . . | 💕 ፍቅርን በቃላት 💕

<<ጠይሙ ባሌ !>>


ክፍል.......8

(በእውነተኛ ታሪክ የተመሰረተ)

አዘጋጅ፦ ፍቅርን በቃላት
.
.
.
"እውነቱን ማወቅ ትፈልጊያለሽ?" አለኝ ካንጋጠጠበት ተመልሶ: የባሰ አጥብቆ እየያዘኝ:: 
"እጄን ልቀቀኝ" አልኩ እንደመታገል እያልኩ:: 
"እንግዲህ ምን የሚያደባብቀን ነገር አለ? ማወቅ ትፈልጊያለሽ ወይ?" በድጋሚ ጮሆ ጠየቀኝ: ፍርሀት ሰውነቴን አንዘፈዘፈው: በአዎንታ እራሴን አወዛወዝኩለት:: 

"ልጆቻችን ከመወለዳቸው በፊት የህይወትሽ እምብርት እኔ ነበርኩ: ትሰጪኝ የነበረው ፍቅርና እንክብካቤ....ኦህህ" አለ አይኑን አቡዞ "ከስራ ስገባ ፈገግታሽን ለማየት እንዴት እቸኩል ነበር" የትዝታ ፈገግታ ላፍታ ፊቱ ላይ ብልጭ አለች::

"ልጆቻችን ሲመጡ ግን ያ ሁሉ እልም ብሎ ጠፋ...በልጆቹ ታጠርሽ:: ሁልጊዜ ደክሞሽ: ሁልጊዜ ተኮሳትረሽ: ሁልጊዜ እራስሽን ጥለሽ ሆነ የማገኝሽ" መሬት መሬቱን አየ "የሚያሙዋሙዋኝ ፈገግታሽን የማየው ከልጆቻችን ጋር ስትጫወቺ ብቻ ሆነና እራሴን አገለልኩ: ለገዛ ቤተሰቤ እንግዳ ሆንኩ" ዝም አለ:: 
"ጨርሰዋ!" አፈጠጥኩበት:: 

"አህህህ...እናት... ሌላ ምን ልበልሽ? የማልወጣው ማጥ ውስጥ ገባሁና አረፍኩት" አይኖቹን ከአይኖቼ አሸሻቸው::
"የምን ማጥ? ፍቅር ያዘህ? ሌላ ሴት አስረገዝክ?" እንደው አፌ ለፈለፈ እንጂ እውነቱን መስማት አልፈለኩም: የቆሰለችው ነፍሴ ልትሸከመው አትችልም: እሱም አልመለሰልኝም::

እጄን ለቅቆ ጃኬቱን ከወንበሩ አንስቶ እየለበሰ 
"እንግዲህ ሁሉም በእጅሽ ነው" አለ ወረቀቱን እያየ "ስልኬን ብትሰጪኝ ደስ ይለኛል: ቁልፍሽ ይኸው" ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው:: ምንም አልተናገርኩም: ከቆምኩበትም አልተነቃነኩም:: 
"ልጠብቅ? ልሂድ?" አለ በሚለማመጥ ድምፅ...የመኪናውን ቁልፍ ከመስቀያው እያወረደ:: አመነታሁ: ስልኩን ያዝኩ አልያዝኩ ዋናው ሰው እየሄደ አይደል:: ባሌ ላይ አፈጠጥኩ...እንግዳ ሆነብኝ:: 
"የቤቱን ቁልፍ ስጠኝ...አንተ ጋ ያለውን" አልኩ እጄን ዘርግቼ:: 
"ም-ን?"

"አሁን ሌላ ቤት አለህ: የቤቴን ቁልፍ ስጠኝ" እጄን አላጠፍኩም "ከዛ ስልክህ የት እንዳለ እነግርሀለሁ"
ጭንቅላቱን እያወዛወዘ አንድ ቁልፍ እጄ ላይ አስቀመጠልኝ:: 
"የጉዋሮውንም" አልኩ እጄን ሳላጥፍ: ሌላ ቁልፍ አስቀመጠልኝ::
"ኦ እረስቼው...የመኪናዬንም" በረጅሙ ተነፈሰና ከቁልፍ መያዣው ጋር እየታገለ በትዝብት አይን አየኝ:: ቁልፎቹን ከተቀበልኩ በሁዋላ ስልኩ ያለበትን ነግሬው በሩ አጠገብ ቆሜ እስኪወጣልኝ ተጣደፍኩ:: 

"ልጆቼን ልሳም?" ሲቃ የተናነቀው ጥያቄው ከምጋልብበት የእልህ ፈረስ በድንገት አፈረጠኝ:: አህህ...ልጆቻችን! ምኑንም የማያውቁት: ምኑም ውስጥ የሌሉበት: ግን ደግሞ ከሁለታችንም በላይ የሚጎዱት ምስኪኖች:: ወደመኝታ ቤታቸው ሲሄድ እንባ ባቆሩ አይኖቼ ሸኘሁት:: 

ይቀጥላል .....



የመወያያ ግሩፑን ይቀላቀሉን
@ethio_lifes_group
@ethio_lifes_group
@ethio_lifes_group


╔═══❖• •❖═══╗
@fkrn_be_kalat
╚═══❖• •❖═══╝
4 any comment
@fkrn_be_kalat_bot
❥❥________⚘_______❥❥