Get Mystery Box with random crypto!

#ሰኔ_30 ዝ ክ ረ - ቅ ዱ ሳ ን | ✞ ፍኖተ ጽድቅ ✞

#ሰኔ_30

ዝ ክ ረ - ቅ ዱ ሳ ን


እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የልደት በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!!!



የአምስት ዓመቱ ህጻን ባህታዊ ቅዱስ ዮሐንስ!
...........................................................................................................................
የዓለም ሁሉ ደስታ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተወለደ
...........................................................................................................................
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ለወላጆቹ የዘገየ የሚመስል ግን ወደር የማይገኝለት ታላቅ ስጦታ ነው።

ወላጆቹ ቅዱስ ዛካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥም በጸሎት የሚተጉ ዘወትር ከቤተ መቅደሱ የማይጠፉ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው። ነገር ግን ልጅ ለምን አልተሰጠንም፣ ጥያቂችንም ለምን በፍጥነት መልስ አላገኝም ባንተ የማያምኑ በቤተ መቅደስህም ለጸሎት የማይቆሙ፣ እልፎች ልጅ ታቅፈው እኛን ለምን ከለከልከን ? ጸሎታችንንስ ለምን አልሰማህም ብለው በእግዚአብሔር ላይ አላጉረመረሙም።

እንዲያውም ቅዱስ ሉቃስ እንደሚነግረን የዘጠና ዓመቷ ኤልሳቤጥና የመቶ ዓመቱ ካህኑ ዘካሪያስ
"በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: ሉቃ 1÷6

እኛ ጠዋት ለምነን ማታ ካልሆነልን ብለን ስንት ዘመን አጉረምርመን ይሆን ?

ሁለቱ ቅዱሳን ግን ቢዘገይም የሚቀድመው የሌለ አምላካቸውን ሙሉ ዘመናቸው ሲያመሰግኑ ኖሩ።

እግዚአብሔርን ጠይቀነው፣ለምነነው ዝም ካለን እጅግ የተሻለ ውድ ነገር ሊሰጠን ነውና በትእግስት እንጠብቅ።

እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ቅዱስ ዮሐንስ የመሰለ ድንቅ ልጅ ለዓለም ሁሉ ደስታ የሚሆን ድንቅ ስጦታ ለመቀበል ዕድሜ ሰጥቶን 1000 ዓመትስ ብንጠብቅ ስ ? በደስታ እንጂ።

እስኪ ተመልከቱ ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ድንቅ ልጅ ሰጣቸው።

ያውም አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረለት ኢሳ 40:3 ሚል 3:1ዐ በቅዱስ ገብርኤል ከመወለዱ አስቀድሞ የተመሰከረለት ሉቃ 1÷14 በሗላም ጌታ ክርስቶስ " እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም " ማቴ 11:11 ብሎ የመሰከረለት ታላቅ ነቢይ ልጅ ተሰጣቸው።

ቅዱስ ዮሐንስ ገና በማህጸን ሳለ የአምላክ እናቱ የእመ ብርሃንን ድምጽ "ሰላምታ" በሰማ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ እናቱ ኤልሳቤጥ በምስጋና እርሱ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘሏል (ሰግዷል)።

በቤተልሔም ህጻናት ላይ የሞት አዋጅ ሲታወጅ ቅዱስ ዮሐንስ 2 ዓመት ከ6 ወሩ ነበር።

" የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ?" ብለው ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን
ክፉው ሄሮድስ አስገደለ። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ...
" ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ።" ማቴ 2:16 ።

ነገር ግን ትንሽ ቆይተው ክፉዎች አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ስለ ዮሐንስ ነገሩት:: እንዲህ በማለት "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" ብለው።

ይህንንም ዜና በእድሜዋ ማብቂያ ውድ ስጦታ የተሰጣት እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ሰማች። ወዲያውም ይዛው ሸሸች።

ቅዱስ ዘካርያስ ግን ካህን ነውና በቤተ መቅደስ መካከል አግኝተው ገድለውታል።

ወንድሞቼ ሆይ መላ ዘመንን ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ እስከ ሞት ድረስ መታመን እንደምን መታደል ነው ?

ጌታ ሆይ እኔ ኃጢያተኛውን ልጅህን ለቤተ መቅደስህ ታማኝ አገልጋይ ሆኜ እኖር ዘንድ ፈቃድህ ትሁን ።

ቅድስት ኤልሳቤጥም በበረሃ ገዳመ ዚፋታ በተባለ ስፍራ ሕጻኑን እያሳደገች ለ5 ዓመታት አብራው ቆየች።
ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ 5 ዓመት ሲሞላው እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች።ሰው የማኖርበት የሰውም ድምጽ በማይሰማበት አራዊት በሰለጠኑበት ዱር የቀኑ ሙቀት የሌሊቱ ግርማ በሚያስፈራበት በዚያ በስተርጅና የተሰጣትን ውድ ስጦታ ከሞት ለማትረፍ በዛለ ሰውነቷ በደከመ ጉልበቷ ተከራታ ከሰው ተለይታ በበረሃ የከተመችው እናቱ ገና በለጋነቱ እድሜ ህጻኑ ዮሐንስን እንደ ታቀፈች የሞት እንቅልፍ አሸለበች።

ይህ የአምስት ዓመት ህጻን በበረሃ ይሰማ የነበረው ድምጽ የእናቱ ብቻ ነበረ። አሁን ግን እርሱም የለም

በዚህ ጊዜ ሕጻኑ ዮሐንስ በበረሃ ውስጥ ምርር ብሎ አለቀሰ። የሚያስደንቀው ነገር እልም ባለው በረሃ በሀገረ እስራኤል በገዳመ ዚፋታ የተሰማው ለቅሶ...

አንድ ልጇን ሄሮድስ እንዳይገልባት የግብጽን በረሃ አቆራርጣ የአሸዋውን ግለት፣ የውሃውን ጥማት ችላ ግብጽ የወረደች እመ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ የህጻኑን ለቅሶ ሰማችው።

ያዘኑትን የምታረጋጊ የእኛ የልጆችሽ ለቅሶ ፈጥነሽ የምትሰሚ እመቤቴ ሆይ ዛሬም የኢትዮጵያ እናቶችን ለቅሶ ሰምተሽ መከራውን በቃ በይን።

ከዚያም እርሷም አንድ ልጇን ታቅፋ ስደት ላይ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ጋር በደመና ፈጥና ከዮሐንስ ዘንድ ደረሰች።

አቅፋም አጽናናችው፣ ከዓይኖቹ የሚወርደውን እንባም አበሰችለት።

ልጇንም ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችንም እናቴ ሆይ "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት።
እመብርሃንም አጽናንታው፣ባርካው ተለያዩ።

ተመልከቱ ይህ አስደናቂ የአምስት ዓመት ህጻን ገና በህጻንነቱ የብህትውናን ህይወት ጀመረ።

የመጀመሪያው የአምስት ዓመት ህጻን ባህታዊ ሆነ

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዚያው በበረሃ የግመል ጠጉር ለብሶ፤ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ለ25 ዓመታት በዚያው ቀጠለ።

የብህትውናን ሕይወት በህጻንነት ዕድሜው በበረሃ የጀመረው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው በቆይታው በንጽሕና በቅድስና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ምን ይደንቅ ምን ይረቅ።

30 ዓመት ሆኖት እግዚአብሔር ከሰማይ ተናግሮ "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ" እስካለበት ድረስ በዚያ ኖረ።

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በረከቱ ይደርብን !

ሼር በማድረግ ለሌሎች አዳርሱ!!
@finote_tsidk
@finote_tsidk