Get Mystery Box with random crypto!

#ተመስገን በላይ በሰማያት ያለህ፣ ከፍ ብለህ የምትከብር፣ የምስጋና መስዋዕት የሚቀርብልህ፣ የማይ | ፍኖተ ~ ጽድቅ

#ተመስገን

በላይ በሰማያት ያለህ፣ ከፍ ብለህ የምትከብር፣ የምስጋና መስዋዕት የሚቀርብልህ፣ የማይቋረጥ አምልኮ የሚደረግልህ፣ ምድርን ያበጀህ፣ ሰማይን የዘረጋህ፣ የሁሉ ገዢ የሆንክ፣ ከዘመን በፊት ገነህ የኖርክ፣ ሁሉም አርጅቶ ዛሬም ያለህ፣ ሁሉን አሳልፈህ ለዘላለም የምትኖር፣ የፍጥረት አስገኚ የሆንክ፣ ሁሉን በፍቃድህ ያበጀህ፣ ይሁን ብለህ የሆነልህ፣ ሁሉን በቃልህ ያስዋብክ፣ የዘመን ቆጣሪዋ የፍጻሜ አዋቂዋ እግዚአብሔር ሆይ ተመስገን። በእኔ የማክበር ጥግ የማትከብር፣ በማንም ምርጫ ስልጣን ያላገኘህ፣ በአመኑህ እልልታ ክብርህ ከፍ የማይል፣ በፍጥረት ዝምታ ምስጋና የማይጎድልብህ፣ በሆታ የማትደምቅ፣ በእጅ ብልጫ የማትሾም ህያው አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ምስጋና ይድረስህ።

ለውለታህ አንዳች የምከፍለው የለኝምና ተመስገን እልሃለሁ። የእኔን መተላለፍ ሳትመለከት የዳግም እድል ዝናብ ያዘነብክልኝ፣ ከከብት በረት በላይ በከረፋው ልቤ ልትኖር ያልተጸየፍክ፣ በኃጢአት የጎረበጠው ሰውነቴ ያልቆረቆረህ፣ ዘወትር የሚስተው ህሊናዬ ያላራቀህ፣ ለተንኮል የተጋው አቅሜ ያላሸሸህ፣ በራሱ መንገድ የሚራመደው እግሬ ያላስቀረህ፣ የአለምን የሚመለከት አይኔ ያልሰወረህ፣ ለአለም ያጨበጨበው እጄ ያልሰበሰበህ፣ ከአንተ ለመራቅ የሚደረግ ጥረት አንተን ያልጎተተህ፣ ይህም ሁሉ ሆኖ ውለታ የምትውል፣ የምትመግብ፣ የምታሳርፍ እና የምታናቃ እሩሩ አባት ነህና ክብር ይሁንልህ።

የቱ ፊደል፣ የቱስ ቃል፣ የቱ ሀረግ፣ የትኛው አረፍተ ነገር፣ የቱ አንቀጽ፣ የቱስ መጽሐፍ፣ የትኛው ጸሓፊ፣ የቱ ተራኪ፣ የቱ አንባቢ፣ የቱስ ምሁር፣ የቱ ገጣሚ፣ የቱስ ሰባኪ፣ የቱ መምህር፣ የቱ አዋቂ የትኛው የቱ.... እኮ የቱ ብርቱ? ውለታህን ሊገልጥ የሚቻለው እኮ ማነው ብቁ? .....ማንም....የለም አባት እግዚአብሔር ሆይ አንተ ህሊናን የሚያልፍ ውለታ ውለህልናል። አዕምሮን የሚሻገር ዋጋ ከፍለህብናል። ምስጋና ያለንን ማቅረባችን እንጂ የሚገባህ ሆኖ አይደለም። እልልታው ዝም ከምንል ብለን እንጂ ውለታህን ይክሰዋል ብለን በፍጹም አይደለም። ሰው ውለታ ቢውልልን በሌላ ውለታ እንክሰዋለን። የአንተ ውለታ እኮ አሳሪ ውለታ ነው ማርኮ የሚያሰቀር፣ ስቦ የሚያቅፍ፣ ይዞ የማይለቅ፣ ጠርቶ የሚያከብር፣ ያለፈውን ዘመን የሚያስጥል፣ የከንቱ የሆነውን የሚያስተው ውለታ ነው። ውለታህ መባዘኔን ያስቀረ፣ መጥፋቴን ያገኘ፣ ትላንቴን የለወጠ ነውና ክብር እና ምስጋና ለአንተ ይሁንልህ። አሜን

ውለታህን ከንቱ በሚያደርግ ኑሮ ውስጥ እንዳልሆን በጸጋህ ደግፈኝ። አሜን

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
ሰኔ 23/2014 ዓ.ም

ይቀላቀሉ ➟ @fenote_tsedek
በቅንነት ያጋሩ ➟ @fenote_tsedek