Get Mystery Box with random crypto!

#ባያድነኝም_እንኳን እግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት እና መደገፍ መቼም መዋዠቅ የሌለበት እና የ | ፍኖተ ~ ጽድቅ

#ባያድነኝም_እንኳን

እግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት እና መደገፍ መቼም መዋዠቅ የሌለበት እና የጸና መሆን እንዳለበት ለሁላችንም ግልጽ ነው። እግዚአብሔር ለታመኑት እና እርሱን ለተጠጉ ዘወትር የእርዳታ እጁ ወደ ኋላ አይልም። እግዚአብሔርን በምቹ ጊዜ ማመን እና አንተ መታመኛዬ ነህ ማለት ለብዙ ሰው ይቀላል ነገር ግን ሁኔታ በላተመቻቸ ጊዜስ?.... ምናልባት ባልደለን ጊዜስ?..

ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 3 ላይ ያለውን አንድ ታሪክ ላስታውሳችሁ ሰዎቹ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎም ይባላሉ ንጉሱ ላቆመው የወርቅ ምስል(ጣዖት) አንሰግድም በማለታቸው ንጉስ ፊት ተገኝተው ይህን ይናገራሉ። ¹⁷ የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ¹⁸ ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።

እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ ሙሉ እምነትን እርሱ ላይ መጣል የአማኝ ተግባሩ ነው ነገር ግን በእግዚአብሔር ያለው እምነት ምክንያት ሆኖ መከራ የሚገጥመው ከሆነ እግዚአብሔር ባለመተው ፈንተ መከራውን አሜን ብሎ ይቀበላል። እነኚህ ሰለስቱ ደቂቅ ያደረጉት ይሄኑ ነው። የእግዚአብሔር እርዳታ ሁሌ የማያጠራጠር ነው እግዚአብሔርን የሚያስክድ ነገር በህይወታችን ቢገጥመን ግን እግዚአብሔርን ከመተው ያለንን ሁሉ ማጣት ይሻላል።

ብዙ ክርስቲያን የሚፈተነው በዚህ ነገር ነው። አብዛኞቻችን በተመቻቸ ህይወት ለመኖር ስንል የዘላለም ምቾታችንን እንተዋለን። ለምድር ድሎት እና ተድላ ስንል ከምድር ጋር ተስማምተን ከሚስማመን እንርቃለን። ክርስትና ያለእግዚአብሔር በመኖር ከማለፍ ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ መሞትን ያስችላል።

ክርስቲያን በህያው በእግዚአብሔር አምኖ እና የእርሱ ልጅ ሆኖ ለምን ይፈተናል ለምን ይቸገራል ለምንስ ይሰቀያል ማለት አንችልም የእግዚአብሔር መሆናችን ለምድሪቱ ፈተና እና የማንመች ስለምንሆን ከምድር የሚደርሰን የመልስ ምት የእግዚአብሔር በመሆናችን የሚመጣ ነው። ከአለም ጋር ተስማምተን ብንኖርማ ይሄ ሁሉ ባልሆነ ወደ ፊትም ምንም ባልመጣ ነበር።

ነገር ግን የክርስትና ባህሪው እየሞቱ መብዛት፣ እየተገፉ ማባብ፣ እየተሰቃዩ ማንጸባረቅ ነውና ከተያን ከሰማያዊው ክብር የተነሳ በሚመጣን በማንኛው ፈተና ወደ ኋላ የምንመለስ አንሆንም። እግዚአብሔር ከማንኛውም ነገር ያደነናል ግን እርሱ እግዚአብሔር ምክንያት ሆኖ በህይወታችን አንዳች ነገር ቢመጣ ከእግዚአብሔር ተለየትን ከሚኖረው ደስታ ይልቅ ከእርሱ ጋር ተጣብቀን የሚመጣብን ሞት ወደ እርሱ መድረሻ መንገዳችን ነውና በጸጋ እንቀበለዋለን። እኛ በሞት ምክንያት ወደ ዘላለም ሞት የምንሄድ ሳንሆን በሞት ምከንያት ወደ ዘላለም ህይወት የምንጉዝ ነንና ሞት ወደ ወደደን ወደ ጌታችን የሚወስደን መንገድ ነው።

አምላካችንን በግርማው የማየት ነፍቆት ውስጣችን ሲሞላ ለሞት ያለን ፍራቻ ይጠፋል። ባያድነንም እንኳን እርሱን አንክድም የማለትን ድፍረት ያለን እንደሆነ የእኛ የሆነው ሁሉ ቢነጠቀን ምንም ግድ የለንም ያለን አንዱ አምላካችንን የሚያስክድ ማንኛው መከራ ግን አንገት አያስደፋንም። በሸንጎም ፊት በነገስታትም ፊት ያለን ምስክርነት ይሄ ነው እርሱን አምላካችንን አንክደውም አንተወውም ከእርሱ ውጪ ለምንም አንሰግድም።

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
ግንቦት 25/2014 ዓ.ም

ይቀላቀሉ ➟ @fenote_tsedek
በቅንነት ያጋሩ ➟ @fenote_tsedek