Get Mystery Box with random crypto!

ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በሀገራቸው የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው ማገዝ ከሁሉም እንደሚጠ | Ministry of Labor and Skills - Ethiopia

ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በሀገራቸው የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው ማገዝ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተገለፀ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጃምቦ የፅዳት አገልግሎት ድርጅት እና ፈርስት ኮንሰልት ጋር በመተባበር በመሰረታዊ የፅዳት አገልግሎት የሰለጠኑ 1ሺህ 86 ከስደት ተመላሽ ዜጎች ስልጠናቸውን አጠናቀዋል።

ሰልጣኞቹ በሀገራቸው ላይ እንዲሰሩ ለተመቻቸላቸው ዕድል ምስጋናቸውን በገለፁበት ሥነስርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ሥምሪት ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ አበራ በተለያዩ ሀገራት የተሻለ የሥራ ዕድል ፍለጋ ከሄዱት መካከል በሳዑዲ ከሚገኙት መቶ ሁለት ሺህ ዜጎችን የመመለስ ሥራው መቀጠሉን የገለፁ ሲሆን፥ እስካሁንም 76ሺህ ዜጎችን መመለስ መቻሉን ገልፀው ለእነዚህ ዜጎች ተባብሮ የሥራ ዕድል ማመቻቸት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል የመመዝገብ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑት ዜጎች የተሰጠው ስልጠና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ስምምነት በመፈፀም ዜጎቹን ወደሥራ ለማሰማራት የተደረገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።

ዜጎቹን በፅዳት ሥራ አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማሰማራት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር እየሰራ የሚገኘው ጃምቦ የፅዳት አገልግሎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ገብርዬ በበኩላቸው ስልጠናው ለሥራ የሚያዘጋጅ መሆኑን ተናግረው ራሳቸውንና ወገናቸውን የሚጠቅሙበት እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ልማት ቢሮ የሥራ ስምሪትና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት አቶ ሰብሃዲን ሡልጣን በከተማዋ ከተመዘገቡት ከስደት ተመላሽ ሥራ ፈላጊ 7ሺህ 280 ዜጎች 1ሺህ ያህሉ ለመጀመሪያ ዙር መሰልጠናቸውን ተናግረው ቀጣይ መሆኑንም አረጋግጠዋል።