Get Mystery Box with random crypto!

ትረፊ ያላት ነብስ አውሮፕላን ተከስክሶ ተርፈው፣ አደገኛው ጫካ ውስጥ 40 ቀን የቆዩት ህፃናት ጉዳ | FastMereja.com

ትረፊ ያላት ነብስ አውሮፕላን ተከስክሶ ተርፈው፣ አደገኛው ጫካ ውስጥ 40 ቀን የቆዩት ህፃናት ጉዳይ እያነጋገረ ነው
#FastMereja
ተሳፍረውበት የነበረው አውሮፕላን በኮሎምቢያ አማዞን ጫካ ውስጥ ተከስክሶ ከአንድ ወር በላይ ጠፍተው የቆዩት አራት ሕጻናት በሕይወት ተገኙ።

ለ40 ቀናት ያህል ጠፍተው የነበሩት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የ13፣ የዘጠኝ፣ የአራት እና የአንድ ዓመት ልጆች ናቸው።

አውሮፕላኑን የተሳፈሩት ከእናታቸው ጋር ሲሆን እአአ በግንቦት 1 ነበር የተከሰከሰው።

እናታቸው እንዲሁም አብራሪውና አጋር አብራሪው በአደጋው ምክንያት ሞተዋል።

የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉዝታቮ ፔትሮ እንዳሉት ልጆቹ ለሳምንታት ከተፈለጉ በኋላ መገኘታቸው መላ አገሪቱን ያስደሰተ ነው።

“ተዓምራዊ ቀን ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ብቻቸውን ነበሩ። ራሳቸውን በሕይወት ያቆዩት በራሳቸው ጥረት ነው። ታሪክ ይዘክራቸዋል” ሲሉም አክለዋል።

“እነዚህ ልጆች የሰላም ልጆች ናቸው። የኮሎምቢያ ልጆች ናቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የአገሪቱ ወታደሮችና ቀደምት ማኅበረሰቦች ልጆቹን ለማዳን ሲረባረቡ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጥተዋል።

ልጆቹ ለ40 ቀናት ጠፍተው ነበር። ሕክምናም እየተሰጣቸው ነው።

ፕሬዝዳንቱ ከልጆቹ አያት ጋር መነጋገራቸውንና አያትየው የልጅ ልጆቻቸውን “እናት የሆነችው ደን እንደመለሰቻቸው” መናገራቸው ተገልጿል።

ወደ መዲናዋ ቦጎታ ሲወሰዱ አምቡላንስ እየጠበቃቸው ነበር።

ሴስና የበረራ ቁጥር 206 ከአማዞን፣ አራራኩራ ተነስቶ ወደ ሳን ሆሴ ዴል ጉዋቫሪ እየተጓዘ ሳለ ነው የሞተር ችግር የገጠመነው።

በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት ሦስት ሰዎች አስክሬን አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ቦታ ተገኝቷል።

ከሲቪል አቪዬሽን የወጣው ቅድመ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ሕጻናቱ ከአደጋው ተርፈው ጫካ ውስጥ ሲኳትኑ ከርመው ነው የተገኙት።

ፍለጋው ከተጀመረ ሳምንታት ተቆጥሯል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ልጆቹ ጥለዋቸው የሄዱ እቃዎች እያገኙ ነበር።

የውሃ ጠርሙስ፣ መቀስ፣ ፀጉር ማስያዣ እና ጊዜያዊ መጠለያ ተገኝተዋል።

ትንንሽ የእግር ዱካዎችም መገኘታቸው ተገልጿል።

እነዚህን መነሻ አድርገው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ልጆቹ በሕይወት እንዳሉ አውቀው ፍለጋው ተካሂዷል።

ጫካ ውስጥ ጃጓር፣ እባብና ሌሎችም እንስሳት ይገኛሉ።

ልጆቹ ሆቶቶ የተባለ ቀደም ማኅበረሰብ አባላት ናቸው።

ማኅበረሰቡ እንደሚለው ልጆቹ በሕይወት እንዲገኙ የረዳቸው ስለ ፍራፍሬ ያላቸው ዕውቀትና ጫካ ውስጥ ራስን የማዳን ክህሎታቸው ነው።

ቀደምት ማኅበረሰቦችም ልጆችን ሲፈልጉ ቆይተዋል። በሄሊኮፕተር የሴት አያቸው ድምጽ ሲተላለፍም ነበር።

በሆቶቶ ቋንቋ ልጆቹ በቀላሉ እንዲገኙ አንድ ቦታ እንዲቆዩ ነበር አያትየው ተናግረው የነበረው።

ባለፈው ወር ልጆቹ መገኘታቸውን ፕሬዝዳንቱ ትዊት አድርገው መረጃው ስህተት ነው የሚል ትችት ተሰንዝሮባቸው ቆይተው ኋላ ላይ ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የተሰጠው መረጃ ያልተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

መረጃው የቢቢሲ አማርኛ ነው

@fastmereja