Get Mystery Box with random crypto!

በዚህ ወቅትም ይሁን በማንኛውም ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ልትጣላት ቀርቶ ልታስቀይማት እንኳ የማይገባ አገር | Fasil Yenealem

በዚህ ወቅትም ይሁን በማንኛውም ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ልትጣላት ቀርቶ ልታስቀይማት እንኳ የማይገባ አገር ብትኖር፣ ኤርትራ ናት። ኤርትራ የሰሜን እዝ በተመታ ጊዜ ከዋለችው ውለታ በተጨማሪ ሱዳንና ግብጽ አብረው ሊያጠቁን በተነሱበት ጊዜ፣ ከጎናችን ተሰልፋ እውነተኛ ወዳጅነቷን አሳይታናለች። የኤርትራ መንግስት የቱንም ያክል ዋጋ ያስከፍለው፣ ያመነበትን ነገር ያለምንም ማወላወል ያስፈጽማል፤ የሚነበብ፣ የሚገመትና የሚታመን የውጭ ፖሊሲ ያራምዳል።

ኤርትራ እና ኢትዮጵያ እጣ ፋንታቸው አንድ ስለሆነ ተከባብረውና ተደጋግፈው መጓዝ ምርጫቸው ሳይሆን ግዴታቸው ነው። ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ፣ ኢትዮጵያም በኤርትራ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸው፣ ጎረቤት ሳይሰማ ቁጭ ብለው ተነጋግረው መፍታት አለባቸው።

መንግስታችን የሚነበብና የሚታመን የውጭ ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል። አንዴ የአፍሪካ ቀንድን እናጣምራለን ስንል፣ ሌላ ጊዜ ፖን አፍሪካኒዝም እናራምዳለን ስንል እንደገና ምዕራባውያን ደጅ ሄደን ስንለማመጥ ስንታይ፣ ሌሎች አገሮች እኛን አምነው ለመከተል ይቸገራሉ። ጠላቶቻችንም ይንቁናል። የውጭ ፖሊሲያችን፣ የአስር፣ የሃያ፣ የሃምሳ ዓመት እየተባለ ሊቀረጽ ይገባዋል። በዘላቂነት የማንፈጽመውን አጀንዳ በስሜት ተነድተን ወይም ለአጭር ጊዜ የፖሊቲካ ትርፍ ብለን፣ ለአንድ ሳምንት አንስተን በሁለተኛው ሳምንት ላይ አንጣለው። ከልብ ያመንበትን አጀንዳ ብቻ ይዘን እስከመጨረሻውን እንጓዝ።

በግሌ በአፍሪካ ጥምረት ( በፖን አፍሪካኒዝም) ከልብ የማምን ሰው ነኝ። የዶ/ር አብይ መንግስት ፖን አፍሪካኒዝምን ማቀንቀን ሲጀምር ከልቤ ተደስቼ ነበር፣ ግን መልሶ አቀዘቀዘውና ሃሞቴን አፈሰሰው። አሁን ፖን አፍሪካኒስቶችን ፍለጋ አይኔን ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ እየወረወርኩ ነው።

ለማንኛውም አፍሪካን ባናጣምር እንኳ ከኤርትራ ጋር እንዳንጣላ መንገዳችን ሁሉ ብልጠትና ጥንቃቄ የተሞላበት ይሁን።