Get Mystery Box with random crypto!

የፋሲል ከነማ ዋና አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ (ቲጋና) ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ገጽ ጋር ቆይታ አድ | ፋሲል ከነማ (አፄዎቹ) እግር ኳስ ክለብ / Fasil Kenema Football Club ™🇦🇹

የፋሲል ከነማ ዋና አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ (ቲጋና) ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ገጽ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

*ፋሲል ከነማ፦ ጤና ይስጥልኝ ኃይሉ ነጋሽ የፋሲል ከነማ ዋና አሰልጣኝ ሆነህ በመሾምህ እንኳን ደስ አለህ እያልኩ ቡድኑን በሀላፊነት በመረከብህ ምን ተሰማህ? ፊርማህ ለአንድ አመት መሆኑ የእግር ኳስ ሀሳብን ለመተግበር የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለ??

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ እንኳን አብሮ ደስ አለን!
ቡድኑን በሀላፊነት በመረከቤ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጠንካራነቱን በዋንጫ ክብሮች ያጀበ ለተከታታይ አመት በአፍሪካ መድረክ ሀገር የወከለ ከምስርታው ጀምሮ ትልቅ በሆነ ክለብ እና ክለቡን የህይወታቸው አካል አድርገው በሚደግፉ ደጋፊዎች ባሉበት ሁኔታ ሀላፊነት ወስዶ መሰራት ያስደስታል።
ሲቀጥል ከልጅነት እስከ እውቀት ላሳደገኝ ክለቤ ከተጫዋችነት ጀምሮ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት መስራት ክብርም ኩራትም ነው እያልኩ የፊርማ አመት መብዛትና ማጠር ሳይሆን በምታስመዘግበው የስኬት ስራህ ነው ቀጣይነትህ የሚረጋገጠው እኔ ደግሞ ለክለቡ አዲስ ሰው ስላልሆንኩ ተፅዕኖ የለብኝም።

*ፋሲል ከነማ፦ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት በስምምነት ከተረከብክ በኋላ ለ2015 የውድድር አመት ዝግጅት ጀምራችኋል ከጀመራችሁ ስንት ጊዜ ሆናችሁ?? ዝግጅታችሁስ በምን አይነት ሁኔታ እየሄደ ይገኛል።

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ ለ2015 ውድድር ዝግጅት ከጀመርን 23 ቀን አስቆጥረናል። የቡድናችን ስኳድ ተሟልቶ ልምምድ ለመጀመር ያልቻልንባቸው ሁኔታዎች የተጫዋቾች ጉዳት እና ለብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ለመስጠት በሄዱ ልጆች እንዲሁም በሀገር ውስጥ የአጥቂ ቦታ ተጫዋች ለማስፈረም ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ የውጭ ሀገር ተጫዋች ለማስፈረም ሂደቱ ጊዜ በመውሰዱ ልጆችን አሟልቶ ዝግጅት ለመስራት ብንቸገርም ባሉት ልጆች ዝግጅታችን በተገቢው መንገድ እየሰራን መጠናል አሁንም ጉዳት የተመለሱትን አዲስ ክለባችን የሚቀላቀሉትን እየጨመርን ልምምዳችን በቀን ሁለት ጊዜ በሜዳ ላይ እና በጅምናዚየም እየሰራን እንገኛለን።

*ፋሲል ከነማ፦ የአፄዎቹን ቡድን በ2015 የውድድር አመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እና በፕሪሚየር ሊጉ በአሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ስር በምን አይነት የእግር ኳስ ሀሳብ እና አቀራረብ እንጠብቀው??

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ በእርግጥ ፋሲል ከነማ ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የራሱ የሆነ ቅርፅ የጨዋታ መንገድ ያለው ቡድን ነው። ሆኖም አሁንም ቢሆን የያዝናቸውን ተጫዋቾች ጥራት መሰረት አድርገን ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወትና ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል የሚደርስ ቡድን ለመሰራት ጥረት እያደረግን ነው።

*ፋሲል ከነማ፦ በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ክለባችን ለዋንጫ ክብር ሲበቃ ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች ጋር ተለያቶ አዳዲስ ልጆች አስፈርመናል ይሄ የቡድን ግንባታ እንዴት ይገለፃል??
ለእግር ኳስ ሀሳብህ መተግበሪያ የሚሆኑ ተጫዋቾችን አሟልተናል ብለህ ታምናለህ?? ከዚህ በኋላስ የተጫዋች ግዥ ይሆረናል??

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ በእርግጥ ለ2015 እቅዳችን ይህ አልነበረም አብዛኛው የክለባችን ተጫዋቾች ውላቸውን የጨረሱ ስለነበሩ መቆየት ያለባቸውን በማቆየት ክፍተት አለብን ብለን ባሰብናቸው ቦታዎች ብቻ ጨምረን መጓዝ ነበር እቅዳችን...አስፈራሚ ኮሚቴዎች ውላቸውን ጨርሰው የምንፈልጋቸውን ልጆች ማቆየት እንዲቻል ከፍኛ ጥረት ቢያደርጉም በተለያዩ ምክኒያቶች አልተሳካም ሆኖም ተጫዋቾች ክለቡን ጠቅመዋል እነሱም ተጠቅመዋል ነገር ግን ማንንም ተጫዋች ያለፍላጎቱ ማቆየት አንፈልግም አዲስ የተቀላቀሉን ተጫዋቾች ክለባችንን የሚመጥኑ ስለሆኑ የተሻለ ነገር እንሰራለን ብለን እናምናለን። የተጫዋች ግዥን በተመለከተ አሁን ባለን ስኳድ ደስተኞች ነን ነገር ግን ፋሲልን ሊመጥን ይችላል ብለን ያመንበት የአጥቂ ቦታ ተጫዋች ካለ ወደፊት የምናየው ይሆናል።

*ፋሲል ከነማ፦ ከታዳጊ ቡድኑ ያደጉ አዲስ ተጫዋቾች አሉ? ከዚህ በፊት ያደጉትን ወጣቶች እድል መስጠት ላይ ምን ታስቧል?? የቡድናችን ስኳድ ጥልቀት እንዴት ነው??

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ያስፈልጉናል ብለን ያመንባቸውን ልጆች ብቻ ነው ወደ ዝግጅት ይዘን የገባነው ነገር ግን ዘንድሮም ልክ እንደሁልጊዜው ከታዳጊ ቡድኑ የሚመጡ ተጫዋቾች ይኖራሉ ያንንም የምናደርገው የዚህን የደርሶ መልስ ጨዋታ ካደረግን በኋላ ወደ ቡድኑ ተቀላቀለው አብረው ይሰራሉ። የቡድናችን ስኳድ ከአምናው የተሻለ ይሆናል ብለን እናምናለን በሁሉም ቦታዎች ላይ አማራጮች አሉ በዛላይ ከታዳጊዎቻችን ትልቅ ጥረት እና መሻሻል እንጠብቃለን እድሉን ለማግኘት ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል።

*ፋሲል ከነማ፦ የአሰልጣኝ አባላቶችህ እገዛ እንዴት ነው? የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ እየደረሰ ነው የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እና ዝግጁ ለመሆን ምን እየተሰራ ነው??

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ በእውነት ነው የምልህ የፋሲል ጥንካሬ ዋናው ስታፉ ነው። ሁሉም ክለብ እንዲኖረው የሚመኘው ሊኖረውም የሚገባ በጣም ጠንካራና ቀና የሆነ ስራህን በሙሉ የሚያቀልልህ ይቻላል እንጂ የማይቻል ነገር የለም ብሎ የሚያሰብ ትልቅ የሆነ የቡድን መሪ ይዘህ ካዛም አለፍ ስትል ይሄ የአንተሰራ ነው ይሄ የእኔ ሰራ ነው የማይባባል ሰታፍ ይዘህ እንዴት ውጤታማ አትሆንም ይሄ ነው የእኛ ትልቁ የውጤታችን ሚስጢር!! ይሄ መተሳሰብና የስራ ፍላጎት ተጫዋቾች ላይ በመወረዱ ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል፡፡

የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ጨዋታችን እየደረሰነው ቢያንስ ከዚህ በኋላ 10 ቀናቶች ይቀራሉ ሥራችንን በአግባቡ እየሰራን ነው ነገር ግን ትልቁ ችግራችን የወዳጅነት ጨዋታዎችን አለማድረጋችን ነው። ቀደም ብለው ዝግጅት ከጀመሩ ክለቦች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን እዚሁ ባህር ዳር ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ለመጫወት ሞክረናል ወደፊትም ለማድረግ ፕሮግራም ይዘናል ይሄ በቂ ነው ብለን አናስብም ባሉት ቀሪ ቀናቶች ውስጥ አንድም ጨዋታ ቢሆን ከተሻለ ቡድን ጋር ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን።

*ፋሲል ከነማ፦ ከፋሲል ከነማ ቦርድ አመራሮች እና ደጋፊዎቻችን ምን አይነት እገዛ ትጠብቃለህ??

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ፦ የክለቡ ቦርድ አመራሮች አቅማቸው በፈቀደ መጠን መስራት ያለባቸውን እያደረጉ ነው ያለው ከዚህ በላይ ክለባችን ለማጠናከር ትልቅ ስራ እንደሚጠብቃቸው እያመንኩ ቡድኑን ለመገንባት በሰሩት ስራ ላቅያለ ምስጋና አለኝ።
ስለ ደጋፊው ምን እንደምልህ አላቅም የውጤታቸን ትልቁ እና ዋናው ተመስጋኝ ደጋፊዎቻችን ናቸው!! ክለባችን እንዲጠናከር ከመፈለግ አንፃር በዝውውር ወቅት ምን ያህል ጭንቀት እንደነበር ሁላችንም ተረድተነዋል አሁንም ቢሆን ቡድኑን የሚያውቁ አብዛኛውን ነባር ተጫዋቾችን ይዘን በመቀጠላችን ከአምናው የተሻለ ቡድን እንዳለን ተረድተው የተሻለ ነገር እንድንሰራ እንደተለመደው የማያራቋርጥ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪየን አስተላልፋለሁ።

ፋሲል ከነማ፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!!

*አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ (ቲጋና)እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።



#ፋሲል_ከነማ_ከክለብም_በላይ_ነው

@fasilkenema_sc_official