Get Mystery Box with random crypto!

ሁሉም የአገሪቱ የንግድ ስርዓት በሙሉ ተበላሽቷል በሚባልበት ደርጃ ላይ ደርሷል ተባለ ሁሉም የአገ | 𝗙𝗔𝗡𝗔 𝗧𝗩 (ፋና)️ ️️

ሁሉም የአገሪቱ የንግድ ስርዓት በሙሉ ተበላሽቷል በሚባልበት ደርጃ ላይ ደርሷል ተባለ
ሁሉም የአገሪቱ የንግድ ስርዓት በሌቦች፣ በኮትሮባንዲስቶችና በሽፍቶች የተተበተበና ስርዓት አልበኝነት የሰፈነበት በመሆኑ፣ በሙሉ ተበላሽቷል የሚባልበት ደረጃ  ላይ መድረሱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል።

ምክር ቤቱ ይህን የገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በትናንትናው ዕለት ባዳመጠበት ወቅት ነው።

በዚህም የሲሚንቶ፣ የጤፍ፣ የምግብ ዘይት፣ የስንዴ፣ የወርቅ፣ የማዳበሪያ፣ እና የሌሎች ፍጆታዎች የንግድ ስርዓት ህግን ባልተከተለ አሰራር የሚመራና ህገወጥ ደላሎች የበዙብት በመሆኑ እጅግ የተበላሸ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በኑሮ ውድነትና በሕገወጥ ንግድ ተማሯል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት፤ የመንግሥት አመራሮች፣ ደላሎችና ባለሀብቶች ተቀናጅተው በፈጠሩት ብልሹ አሰራር ሕዝቡ እየተጎዳ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለውም፤ ትናንሽ ነጋዴዎች በትልልቅ ነጋዴዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ደላሎችን መቆጣጠር ባለመቻሉም ሕገወጥነት የበላይነትን ይዟል ብለዋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደምም በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ የተደራሽነት ፍትሃዊነት እና የዋጋ ችግር መኖሩን ለመስሪያ ቤቱ ቢገልጽም ችግሩ አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው ብሏል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሲሚንቶ ምርት አዲስ አበባን ጨምሮ በኹሉም ክልሎች እየቀረብ አለመሆኑንና ገበያ ላይ ያለውም በተጋነነ ዋጋ መሸጡን ቢኮንንም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፋብሪካዎች ካለው ፍላጎት አንጻር ከአንድ ሦስተኛ ያልበለጠ እያቀረቡ በመሆኑ፣ አቅርቦትና ፍላጎቱ እስካልተጣጣመ ድርስ ችግሩ የሚዘልቅ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ዋነኛ ተልዕኮ ጤናማ የተረጋጋ የአገር ውስጥ ብሎም የጠረፍ ንግድ ስርዓት መፍጠር ቢሆንም፣ ህግወጥ ንግድና ኑሮ ውድነት በከፍተኛ ሁኔታ በመባባሱ ይህ ተቋም አለ ወይ የሚያስብል ጥያቄ እንደሚፈጥር በምክር ቤቱ አባላት ተጠቅሷል።

"ማን ኮንትሮባንድ እንደሚሰራ የተጣራ መረጃ የለም" ያለው ምክር ቤቱ፤ በንግድ ስርዓቱ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ባለመኖሩ አብዛኛው የንግድ ማህበረሰብ የንግድ ፈቃዱን እየዘጋ ወደ ሕገወጥ ንግድ እየተቀላቀለ ነውም ብሏል።

በዚህም ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሀብታም የሆኑና በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ነጋዴዎች መኖራቸው ተመላክቷል።

ስለሆነም በዚህ ልክ የተበላሸው የንግድ ስርዓት ባስከተለው ጥፋት የተቋሙ አመራሮች "ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ ናችሁ ወይ?" የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል።

ምክር ቤቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ11 ወራት አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው ሲል ገልጾ፣ ባለበት የበጄት አጠቃቀም ችግር ለአብነትም ሥራ ላይ መዋል እያለበት ሳይውል የቀረ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መኖሩን ጠቅሷል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተለይም የመሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ መናር በዓለም አቀፍ እና አገራዊ ችግሮች የተከሰተ መሆኑን ጠቅሶ፤ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ወስዶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

እንዲሁም የፍጆታዎችን ዋጋ ለማረጋጋትና ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጣር የተለያዩ እርምጃዎችን ወስጇለሁ ያለው ተቋሙ፤ በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚታየው ችግር በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን በብዙ ተቋማት ርብርብ የሚፈታ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።