Get Mystery Box with random crypto!

'መርሳት እና ማስታወስ' . . . 'ጠቅላይ ሚኒስትሩ' ሲባል ምን ትዝ ይለናል? ንግግራቸው? ፈገ | GRACE FAMILY

"መርሳት እና ማስታወስ"
.
.
.
'ጠቅላይ ሚኒስትሩ' ሲባል ምን ትዝ ይለናል? ንግግራቸው? ፈገግታቸው? አመራራቸው? ሰላምታቸው? ወይስ ምናቸው? የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንዳ ሞዲ ትዝ አይሏችሁም መቼስ።
አትሌት ኃይሌ ገ/ ስላሴ ሲባልስ ምን ትዝ ይለናል ሩጫው? ዝናው? ሃብቱ? ሆቴሉ? ሜዳሊያው? ሳቁ? ንግግሩ? ወይስ
"ዌል እንግዲህ?" ሁ ?
እንዲህ የሚባል ኢትዮጵያዊ አትሌት አላወቅም የሚለኝ ይኖራል ?

ስለ ሁለቱም የምናወቀው የተወሰነ ነገር በመኖሩ ... ፈጥኖ ወደ ጭንቅላታችን የሚመጣ ማንነት አላቸው በትክክል ይግለፃቸውም አይግለፃቸውም።
እግዚአብሔር ሲባል ምን ትዝ ይለናል? ሰማይ? ምድር? ጨረቃ? ፀሐይ? ሰው?ቤተክርስቲያን ?
በምኑ ይሆን የምናስታውሰው?
የሆነ ጊዜ እንዲህ አለ ...
"ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ ስለዚህ … ረሱኝ"
እነዛ ረሺዎች " እግዚአብሔር" ሲባሉ
ምን? ማን? የቱ? ብለው ሌላ ከስሙ ሌላ ማስታወሻ ምልክትን ይሻሉ ፡፡
ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ "ቆንጆ ጌጧን ሙሽራ ልብሷን (ቬሎዋን አለ አንዱ ሰባኪ በደንብ ሲያስረዳ) ትረሳለች? ህዝቤ ግን ለማይቆጠሩ ወራት ረሳኝ"አለ
የጥር ማለቂያ ላይ ስለ ቬሎ ብናወራ ሩቅ አይሆንብንም
ቬሎ ምንድነው ? ማነው ያመጣው ? ሴት ሙሽራ ሁሉ ቬሎ ትልበስ ያለው ማነው? ለመቆም አይመች ለመቀመጥ ... ለመነካት ተፈርተሽ ለመታቀፍ እርቀሽ ... ብቻ መቼም ይምጣ ሙሽራን ያለ ቬሎ ማሰብ ይከብዳል ወይም ሌላ የሙሽራ ልብስ

እነዚህም "እግዚአብሔር" ሲባሉ
"ማን ነበር?" ብለው ይጠይቃሉ "ያ እንኳ ከግብፅ ያወጣን አምላክ" ሲባሉም የሚያስታውሱት አይመስለኝም
"ጥ ጥ ይቅርታ አላስታወስነውም" ይላሉ
"መናን ያበላን" እ እ የሆድ ጉዳይ ላይ በጥቂቱ ሊያስታውሱት ይሞክራሉ መልሰው ይረሱታል፡፡
እርሱ ግን ስለ እነርሱ ሲጠየቅ
"ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ" ይላል ደግሞም "ሴት ከማህፀኗ የወጣውን ትረሳለች እስከማታስታውሰውስ ትጨክናለች አዎ ትረሳ ይና እኔ ግ አልረሳሽም በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ" ነው መልሱ ።

የጉዳዩ እጅግ አስገራሚነት እዚህ ላይ ነው ይህ ትንሹ ሰው በዚህች ሚጢጢ ጭንቅላቱ ያቅሙን ያህል ጉዳይ አጭቆ ለማስታወስ እየጣረ ... ፎርሙላ እየሸመደደ ፤ የታክሲ መልስ እየተቀበለ፤ ቁርስ ምሳ እራቱን ሳይረሳ ፤ ከረቫት ማሰሩን ሳይረሳ ፤ ኩል መቀባቷን ሳትረሳ … እግዚአብሄርን ያህል ታላቅ እና ትልቅ አምላክ ሲረሳ፡፡

እሱኮ... ዩኒቨርስን ለአፍታ ሳይዛባ እየተቆጣጠረ ፤ የምድርን እና የሰማይን ፍጥረታት ስርአት አስይዞ እያስወጣ እያስገባ ፤ ለፀሀይ ቀንን ፤ ለጨረቃ ከዋክብት ለሊትን መድቦ ፤ ምድርን መስርቶ ፤ መስፈሪያዋን ወስኖ ፤ ለባህር ማእበል ገደብን አበጅቶ ፤ ዝናብን እያዘነበ ከዋክብተትን እያሰረ ሲፈታ … ምኑ ቅጡ! በዚህ ሁሉ ስራ በዚህ ሁሉ ፋታ ማጣት ትንሹን ሰው ማሰቡ አለመርሳቱ፤ "ረሳኋችሁ" ቢል እኮ በቂ ምክንያት አለው፡፡
"ለፈረስ ጉልበቱን ስሰጥ ፤ አንገቱን ጋማ ሳለብስ" ሊል ይችላል
"የሚያግዘኝ እንደሁ የለ ፅንስን በማህፀን ስገጣጥም" ረሳኋችኁ ቢል ያሳምናል፡፡
"እናንተ ደግሞ እነማን ናችሁ? መቼም በምድር ላይ ስንት እና ስንት ቢልዮን ህዝብ የሚጠጋ ህዝብ ነው የሚርመሰመሰው" ቢል እውነቱን ነው። ሰው ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሄር ግን አንድ ነው ፤ አልረሳንምና አላለም።

እንደ ዳዊት እጠይቃለሁ
"አቤቱ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው
ትጎበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው?"
ለራሴም እጠይቃለሁ
"ሰው ሆይ እግዚአብሔርን ትረሳ ዘንድ አንተ ማነህ?"
ለአብረሃም እና ለዘሩ ለዘለአለም ምህረቱ ትዝ እያለው ቅዱሱን ኪዳን አሰበ። ቃሉን አሰበ። እውነቱን አሰበ፡፡
ካልካድን በስተቀር የእግዚአብሄርን አስታዋሽነት መፅሐፍ ቅዱስና ታሪክ ይነግሩናል፡፡
በአመፀኛ ትውልድ መካከል የተገኘው አንዱ ኖህ አምላኩን ሰምቶ በሰራው መርከብ ቤተሰቦቹን ካስመለጠ በኋላ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳንን ተቀበለ፡፡
ዳግመኛ በምድር ዘመን ሁሉ መዝራት እና ማጨድ ፤ ብርድና ሙቀት በጋ ክረምት፤ ቀን እና ለሊት እንዳያቋርጥ በልቡ ካሰበ በኋላ ለኖህ አለው፡፡ ቃል ኪዳኔን ከእናንት በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋ አቆማለሁ አለ፡፡
አዎ አቁሟል፡፡

ዘርቶ የማያጭድ ገበሬ ማን አለ? ክረምትና በጋ ቀንና ለሊትስ መቼ ተቋርጠው ያውቃሉ? እርሱ እግዚአብሄር ቃሉን አይረሳምና።
ከባርነት የወጡ እስራኤላውያን ...
'ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ' ማለቱን ዘንግተው ፤ የራሳቸውንም ቃል ረስተው ጥጃ ሊሰሩ ወርቆቻቸውን ከጆሯቸው ሲያወልቁ ግን ገና 40 ቀንና 40 ሌሊት ብቻ ነበር ያለፈው፡፡

"ህጉን እና ስርአቱን ባለመጠበቅ አምላክህ እግዚአብሔርን እንዳትረሳው ተጠንቀቅ" ቢባሉም አነርሱ ግነ ሊያስተውሱት ከቶ አልቻሉም። ከርሱ ይልቅ የግብፅ ዱባና ሽንኩርት ትዝ ይላቸውና ጣእሙም በአፋቸው መአዛው ባፍንጫቸው እየመጣ ምራቅ ያስውጣቸው ነበር ፡፡
እግዚአብሔር ግን እነርሱን ከማጥፋ በፊት ለአባቶቻቸው የማለላውን ባሪያዎቹን አብርሃምንን እና ይስሃቅ ፣ እስራኤልን አስቦ ራራላቸው፡፡ ዳግመኛ ማደሪያውን በመካከላቸው አደረገ። ምክንያቱም ሳሩ ይደርቃል አበባውም ይግፋ የአምላካችን ቃል ግን ለዘለአለም ፀንታ ትኖራለች፡፡

የ Solomon Abebe Gebremedhin "የዱባ ጥጋብ " መፅሐፍ ምርቃት ላይ የቀረበ !

ጽጌሬዳ ጎንፋ