Get Mystery Box with random crypto!

በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ዛሬ ይኸን ቃል እንደ ገና አነበብሁ። “እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ | GRACE FAMILY

በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ

ዛሬ ይኸን ቃል እንደ ገና አነበብሁ። “እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም፥ አይጮኽምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ” (ኢሳ. 42፥1-4)።
.

እንደምታውቁት፥ በኀጢአት ስንዋከብ ኖረናል። …

በሰው ልጆች መካከል የሚገማሸሩና ለትከሻ ቀርቶ ለጆሮ የሚከብዱ ሰቀቀናም የጥቃት፥ የበደል፥ የግፍና የርኵሰት ሸክሞችን መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን፥ የኾነውን ኹሉ ትተን፥ እኛ የምናውቀውን እንኳ መተረኩ ያደክማል። ዋናውን ጕዳይ ግን ዘልለነው አንኼድም፤ ከዚህ ኹሉ የመንኰታኰት አዘቅት ውስጥ ወርውሮ የዶለን ምንድን ነው? ኀጢአት ነው። በመተላለፍ ጦስና በዐመፃችን መታለል የተሰባበርን እንክልካዮች ኾነናል፤ በእግዚአብሔር መልክ የተሠራንበት ዐላማ ደምቆ እንዳያበራ በውድቀት ጦስ ተዳፍነን የምንጤስ ሻማዎች ነበርን። ሕግ የተሰጠውም ኾነ ሕግን በነቢይ ያልተቀበለው አረማዊ “ኹሉ ከኀጢአት በታች እንደ ኾኑ” በአንድነትና በይፋ ተከስሰዋል (ሮሜ 3፥9)። ማን ተርፏል?
.

የሕይወታችን ቅስም በዘላለም ብርታት እንዲታደስ ቤዝዎታዊ ትድግና አስፈልጎናል፤ እንደ ገና እንድንቆምና በብርሃኑም ብርሃንን እንድናይ ስለ እኛ ኾኖ የሚፈስ የሕይወትን ምንጭ ያስፈልገናል። ውርደታችን ጥልቅ ስለ ኾነ አዳኛችን ምርጥ መኾን አለበት። በብርቱ ስለ ተሰበርን ድንቀኛ በኾነ መንገድ መጠገን አስፈልጎናል። ይህን እውን ለማድረግም እግዚአብሔር ምርጡን ብላቴናውን አዘጋጅቶ ወደ ዓለም ልኮታል። “እኛም አይተናል፤ አባትም ልጁን የዓለም መድኀኒት ሊኾን እንደ ላከው እንመሰክራለን” (1ዮሐ. 4፥14)።
.

እግዚአብሔር ፍጥረት ኹሉ እንዲመለከትለት የሚፈልገው እውነት አለው። አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ በኋላም በሐዋርያው ማቴዎስ አማካይነት ትኵረታችንን በመቀስቀስ ዓለም ኹሉ ወደ ምርጡ ብላቴና እንዲመለከት ይጣራል። መሲሑ ከእልፍ አቻዎቹ መካከል የተገኘ አለቃ አይደለም፤ ብቸኛው ምርጥ ነው። ወደር የለሽ አንድያ ነው፤ አንድዬ ነው። እግዚአብሔር “ምርጤ” ብሎ ይጠራዋል። ለእኛም ዋጋ የማይተመንለት ውድ-ብርቅ-ድንቅ ዕሴታችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኾነ።
.

ምርጡ መሲሕ ደግሞ፥ ሸክማቸው የከበደባቸው ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡና እንዲያሳርፋቸው “በመንፈስ ድኾች” ለኾኑ ኹሉ በግልጽና በይፋ ጥሪውን አቅርቧል። ጥሪውም፥ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ኹሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ. 11፥28) የሚል ነበር። “ተወለደ” ማለትን ስናስብና ስናከብር ይኸን እያሰላሰልን ነው። የዓለሙ ቤዛ ተወለደ። ሲወለድ ለቤዛነት ይሰቀል ዘንድ ነው። ሲሰቀልም እኛን ለማጽደቅና ለመሻር በትንሣኤ ክብር ይነሣ ዘንድ ነው። ትንሣኤውው ዳግመኛ መገለጡን ያረጋግጣል። እነሆ በቶሎ ይመጣል።
.

“ቤዛ ኵሉ ዓለም ዮም ተወልደ” እንደምንል ኹሉ “እግዚእ ኵሉ ዓለም ይመጽእ ካዕበ” እንለለን።
.

መልካም በዓል።
ሰለሞን አበበ