Get Mystery Box with random crypto!

'ገንዘብን የሚቀሙ በተወገዙባት ምድር ሕይወትን የሚቀሙ ፣ የሰው ዘር ቅነሳ የሚያደርጉ ግፈኞች ሲን | "ልጆቼ የቤተክርስቲያንን ነገር አደራ"

"ገንዘብን የሚቀሙ በተወገዙባት ምድር ሕይወትን የሚቀሙ ፣ የሰው ዘር ቅነሳ የሚያደርጉ ግፈኞች ሲንጎማለሉ ማየት ያሳዝናል" ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)


++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ በዛሬው ዕለት በልዩ ጽ/ቤታቸው አማካይነት ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ገንዘብን የሚቀሙ በተወገዙባት ምድር ሕይወትን የሚቀሙ ፣ የሰው ዘር ቅነሳ የሚያደርጉ ግፈኞች ሲንጎማለሉ ማየት ያሳዝናል ሲሉ ገልፀዋል።


ቅዱስነታቸው ስሜትን በሚወርር ልብን በሚያሳዝን፣ ጉልበትን በሚሰብር ኀዘን ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን ፤ ትናንት ባለ ብዙ ቤተሰብ ዛሬ ሌጣ ለሆኑት ፣ የክብር ሞትና መቃብር ለተነፈጉት ሰው ሆነው በሰው ለተገፉት ፣ ኢትዮጵያዊ ሁነው በኢትዮጵያውያን ለተሠዉት ፣ አገር ሳላቸው እንደ ባዕድ ለተቆጠሩት ፣ ለደከሙበት ምድር በወርቅ ፈንታ ሰይፍ ለተከፈሉት ልጆቻችን እግዚአብሔር ያጽናችሁ በማለት ፣ የሞቱትንም ደመ አቤልን ያከበረ አምላክ ደማቸውን እንዲመራመር እንለምናለን ብለዋል።

ብዙ መልካም ቃላት በሚነገሩበት፣ የጥበብ ድምፆች በሚያስተጋቡበት ፣ መሠረት ፈርሶ ለጉልላት ጌጥ በምንጨነቅበት በዚህ ዘመን ፣ እንዴት ካለው ጊዜ ደረስን?" ማለት መመጻደቅ ባይሆን ኖሮ የሚባልበት ወቅት ሁኖ አግኝተነዋል። ትናንት ገንዘብን የሚቀሙ “እንዴት የሰውን ልፋት ይወስዳሉ? ተብለው በተወገዙበት ምድር ሕይወትን የሚቀሙ፤ የሰው ዘር ቅነሳ የሚያደርጉ ግፈኞች ሲንጎማለሉ ማየት ያሳዝናል። ንጹሐን ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነት ብቻ ሲሞቱ ስናይ የዝቅታችንና የመውደቃችን ልክ ማጣት ጎልቶ ይታያል። በርግጥ የሞቱት ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸውና ቤተ ክርስቲያን ትዘክራቸዋለች። ሰማዕት ስለ እግዚአብሔር ብሎ የሚሞት ነው። እነዚህም ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነት ፣ ለምን እንዲህ ተፈጠራችሁ ተብለው የሞቱ ናቸውና ሰማዕታት እንላቸዋለን። ገዳዮችም ቀጥተኛ የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎች ናቸው ነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ

በወለጋና በጋምቤላ የአገራችን ክፍል የደረሰውን አሰቃቂ የወገኖቻችን ግድያ ስሰማ እንደ ወትሮው ልቤ በታላቅ ኀዘን ተመትቷል። በመላው የሀገራችን ክፍልም ክረምቱ ዓመት ከዓመት ጠሉም የንጹሐን እንባ ሁኖ፣ “ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ" ያለው የጌታችን ቃል ደርሶ እያየን ነው። ጆሮ ከአቅሙ በላይ በሚሰማበት በዚህ ዘመን ያላችሁ ልጆቻችን አሁንም ልባችሁን እንደ ነቢዩ ዳዊት በእግዚአብሔር አበርቱ። ጠብና ክርክሩ እግዚአብሔር ከፈጠረው ሰውነት ጋር ነውና እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚሰጥ እናምናለን። የሃይማኖት አባቶችም የምናስተምረው ሕዝብ አልቆ ማንን ልናስተምር መሆኑን ደግመን ማሰብ ያስፈልገናል። አገራችን ኢትዮጵያ የሚያስከብሯትን መሪዎች አሁንም እየተጣራች ነውና መንግሥትና ሕዝብ ግፍን በተግባር ማውገዝ ያስፈልጋቸዋል። ነቢዩ ኤርምያስ በኀዘን ልቅሶው:- የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ ብሏል ሰቆቃ ኤር 4፡1/ የሰው ልጅ ሕያው የእግዚአብሔር መቅደስ ነውና በየስፍራው ሲገደልና ቀባሪ ሲያጣ ስናይ ከነቢዩ ጋር ለማልቀስ እንገደዳለን።

ጊዜው እየረፈደ፣ ሞትም ዜና እየሆነ፣ ዜጋም ክብሩን እያጣ፣ ሥጋትም ገዥ እየሆነ የምንቀጥልበት ጊዜ እንዲያበቃም ታላቅ ጥሪያችንን በሕያው እግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ሲሉም ቅዱስነታቸውን አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

#Ethiopia 
#Tewahedo_Media_Center
#TMC