Get Mystery Box with random crypto!

(ልብን የሚነካ ፀሎት፣ ሁሌ ይህንን እያልን እንለምነው) በአቡነ ሺኖዳ ስለጸሎት ምክር 'መልካ | "ልጆቼ የቤተክርስቲያንን ነገር አደራ"

(ልብን የሚነካ ፀሎት፣ ሁሌ ይህንን እያልን እንለምነው) በአቡነ ሺኖዳ

ስለጸሎት ምክር

"መልካም ነገሮች ከሚባሉት መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቆ መያዙ እና መጠበቁ ነው። እግዚአብሔር ብዙ ቃል ገብቷል እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ግልፅና ታማኝ ነው። እናም ቃሉን አያጥፍም። የእርሱን ቃል ይዛችሁ ከእርሱ ጋር ተነጋገሩ። " ቃል የገባህልንን መች ነው የምትፈፅምልን" በሉት።
ቃልህን ይዤ እጠይቅሀለው “አዲስ ልብን እሰጣችኋለው” ብለሃል ፣ ታዲያ የታለ አዲሱ ልብ? እኔ ራሴን ስመለከተው የድሮ ልቤ እንዳለ ነው። የትናንትናው መጥፎ ጠባይ ልክ እንደ ትናንትናው ነው። የታለ ታዲያ አዲስ ልብ እሰጥሃለሁ ያልከኝ? እኔ ማወቅ እፈልጋለው፣ ከውስጥ እንድትቀይረው እንድትሰማው እፈልጋለው፣ እኔ አስቸገርኩህ አንተ አስተካክለኝ፣ ሥራብኝ፣ ደረቅ መሆኔን አስተካክልልኝ። ስህተት አለብኝና ስህተቴን አስወግደው። ድርቅና አለብኝና ድርቅናዬን አስወግደው ። ኃጢያአት አለብኝና ኃጢአቴን አስወግደው። ጌታ ሆይ እኔ ውስጥ ሥራ ። እናም ውስጤን አንጻው። መጋዙን መዶሻውን አንሳው። ሥራብኝ ይህ መጥፎ እንጨት የተባለውን ላንተ ወንበር አርገው" በሉት።
አንዳንድ ሰዎች ደካማ መሆናቸውን ሲያውቁ አለመቻላቸውን እና መውደቃቸውን ሲያረጋግጡ እግዚአብሔር ወደ ሕይወታቸው እንዲገባ ከመለመን ይልቅ እግዚአብሔርን ይቀየሙታል እና ይጮሀሉ" ለምንድን ነው እግዚአብሔር ብቻዬን የተወኝ? በቃ ከአሁን በኋላ እግዚአብሔርን አላቅም! ቤተክርስቲያን አልሄድም ! ንስሐ አልገባም ! አልቆርብም !" ይላሉ ። ይህ ምንድን ነው? ጌታን ከመለመን ይልቅ መቃወም ይሻላልን?
እስቲ አስተዋይ ሰው እንሁን!
ከእግዚአብሔር ጋር ሆነህ ተፋለም ፣ ታሸንፋለህ እና ታልፋለህም። እግዚአብሔርን እንዲህ ብለህ ጠይቀው...
"ጌታ ሆይ አጋዥ ትባላለህ ፤ አጋዥነትህ የት አለ? ና አግዘኝ። አዳኝ ትባላለህ፤ የት አለ ማዳንህ? ና አድነኝ። ምንም ነገር አይሳንህም ትባላለህ እኔን ማዳን አይሳንህም፥ ያለምክንያት ‘ምንም የማይሳነው’ አንልህምና። ጌታ ሆይ፥ እኔ አንድ ችግር ነኝ። ፊት ለፊትህ ቀርቤያለው መንፈስህን አኑርብኝ። ምንም አይሳንህም እና እኔን ሥራኝ። እምነትህ ደካማ ነው ካልከኝ ፥ ጠንካራ አድርገው። ልቤ ቆሽሿል እና አፅዳልኝ። ሙሴ ጸሊምን እና ማርያም መግደላዊትን እንዳስተካከልካቸው እኔንም አስተካክለኝ። አንተ የምትለው "ወደ እኔ የመጣውን ወደ ውጪ አላስወጣውም " ነው ... ይኸው ወደ አንተ መጥቻለው ባዶ እጄን አትላከኝ ። ጌታ ሆይ የበጎ ነገር ፈጣሪ ትባላለህ እንዲ ከሆነ በእኔ ውስጥ በጎ ነገርን ስራ ።

ከብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ስብከት የተቀነጨበ