Get Mystery Box with random crypto!

#መስከረም_29 #ሰማዕት_ቅድስት_አርሴማ በዚችም ቀን ከቅድስት አርሴማና ከእመምኔቷ ከአጋታ ጋር | ✟የማለዳ ፀሀይ✟

#መስከረም_29

#ሰማዕት_ቅድስት_አርሴማ

በዚችም ቀን ከቅድስት አርሴማና ከእመምኔቷ ከአጋታ ጋር ደናግል በሰማዕትነት አረፉ። ይህም እንዲህ ነው በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን እርሱ መልኳ ውብ የሆነ ብላቴና ድንግል ሊአገባ ሽቶ በየሀገሩ ሁሉ ሒደው መርጠው ያመጡለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ።

ይችንም የሚመስላት የሌለ ቅድስት አርሴማን በሮሜ አገር በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ አገኙዋት። ሥዕሏንም ሥለው ለንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ላኩለት ንጉሡም ሥዕሏን በአየ ጊዜ እጅግ ደስ አለውና ለሠርግ እንዲመጡ ወደ መኳንንቱ ላከ።

እሊያ ደናግልም ይህን ነገር በአወቁ ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ ድንግልናቸውንም ይጠብቅ ዘንድ አልቅሰው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ። ከዚህም በኋላ ተነሥተው በሥውር ሸሹ የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደ ሆነ ወደ አርማንያ ሀገርም ደርሰው በአንድ ቦታ ተቀመጡ ከእርሳቸውም ጋር የተሰደዱ ቁጥራቸው ሰባ አምስት የሆነ ወንዶች፣ ሴቶችም ሠላሳ ዘጠኝ የሆኑ ከእርሳቸው ጋራ አሉ። ምግባቸውን አያገኙም ነበርና በታላቅ ችግር ውስጥ ኖሩ ከእነርሱም መብራት የምትሠራ አንዲት ሴት ነበረች ከእርሷም የእጅ ሥራ ከሚገኘው በየጥቂቱ ይመገባሉ።

ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ስለርሷ ሰማ። ደግሞ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ ስለርሷ ከዲዮቅልጥያኖስ ሸሽታ እንደ መጣች የአርሴማን ሥራ ነገሩት እርሱም አንዱን የአርማንያ መኰንን ለእኔ ጠብቃት ወደ እኔም ላካት ብሎ አዘዘው።

ደናግሉም ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ ተሠወሩ ወደ ንጉሥም ወነጀሉአቸው ንጉሡም ቅዱስት አርሴማን በክብር አድርገው ያመጧት ዘንድ አዘዘ እርሷም ወደ እርሱ መምጣትን እምቢ በአለች ጊዜ እየጎተቱ ወስደው ወደርሱ አደረሷት።

የቅድስት አርሴማንም ላህይና ደም ግባቷን በአየ ጊዜ ድንግልናዋን ሊያረክስ ሽቶ እናቷ አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት አጋታም ወደርሷ ሒዳ ልቧን አስጨከነች እንዲህም አለቻት። ዕወቂ ይህ ርኲስ አረሚ እንዳያረክስሽና ሰማያዊ ሙሽራሽን እንዳትተዪ እርሱም ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር ልጅ ሕያው ክርስቶስ ነው።

ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ ድንግል አርሴማን ያዛት። በዚያንም ጊዜ በቅድስት አርሴማ ላይ የእግዚአብሔር ኃይል አደረባትና በምድር ላይ ጣለችው እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለ ነበር በታናሽ ሴት ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ። ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት ከዚህም በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው አጋታ ጋር ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ።

አንዲት የታመመች ድንግል ነበረች በዐልጋዋ ላይም እንደተኛች ወደ ወታደሮች ጮኸች መጥተውም እንደ እኅቶቿ ራሷን ቆረጡ ሁሉም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነዚያንም ከሮሜ አገር አብረው የመጡ ወንዶችን ገደሏቸው ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ናቸው ሥጋቸውም በተራራ ላይ የተጣለ ሁኖ ቀረ።

ሰማዕታትም ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወደርሱ መጥቶ በላዩ ጸልዮ እስከ አዳነው ድረስ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። የቅዱሳን ሰማዕታትንም ሥጋቸውን ከተጣለበት ሰብስበው በአማረ ቦታ አኖሩአቸው ያማረች ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራችላቸው። ከእነርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕት ቅድስት አርሴማ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም)
https://t.me/joinchat/D8TC9g_CJ-plM2U8