Get Mystery Box with random crypto!

የብጹዕ ዶክተር አቡነ ኤርምያስ መልእክት ................................... | የተዋሕዶ መረጃ

የብጹዕ ዶክተር አቡነ ኤርምያስ መልእክት
.....................................................
ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በተወካያቸው አማካኝነት ተቀብለዋል።
ብጹዕነታቸው ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ከሀገር ውጭ በመሆናቸው መገኘት አልቻሉም።

ብጹዕነታቸው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ባበረከቱት ታላቅ አበርክቶ ነው የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው።

ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ ካሉበት ኾነው ባስተላለፉት መልእክት የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ለእኔ ሳይሆን በጸሎት ሲጠብቁኝ ለነበሩት ለብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ከጎኔ ኾነው በምክር ለረዱኝ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሚፋጠኑት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ድልድይ ኾነው ላገናኙኝ የመስጊድ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለተወጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ነው ብለዋል።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ይሄን ስጦታ ሲሰጥ ማኅበረሰቡን እየሸለመ እንደሆነ እረዳለሁ ነው ያሉት። ስላደረገው መልካም ስጦታም ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል።

ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክትም ኢትዮጵያ ከዚህ የደረሰችው ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ጭምር ሰጥተው፣ መስዋእት አድርገው ነው፣ አንድነቷ ተከብሮ፣ በነፃነት ደምቃ፣ ለአፍሪካውያን የኩራት፣ የክብር ተምሳሌት ኾና የቆየችው በዚህ መንገድ ነው ብለዋል።

አልተማሩም ያልናቸው ወገኖቻችን በመስዋእትነት ያቆዩዋትን ሀገራችንን ተማርን ያሉ ሰዎች በየቀኑ የመለያየት፣ የማፍረስ ፈጠራ እየፈጠሩ ወገንን ከወገን ሲለያዩ፣ የተገነባውን ሲያፈርሱ እየተመለከትን ነው ብለዋል። የጥፋት ተቃራኒ የሆነውን ልማት እንድታለሙ፣ ራሳችሁን ረድታችሁ ሀገራችሁን እንድትረዱ፣ አንድ የሆነችው ሀገራችሁና ሕዝባችሁ በአንድነቱ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ ብለዋል።

የዛሬ ዓመት በመከራ ውስጥ የነበረው ሕዝብ አሁንም ተበድሮ የዘራው ገበሬ አርሞ መሰብሰብ እንዳይችል፣ የጦርነት ቀጣና ኾኗል፣ የዚያ ገበሬ ቤት እየፈረሰ ነው፣ ሕይወት እየታጣ ነው ብለዋል። ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥም ጠይቀዋል። "
መምህር ኤፍሬም ሀብተ ማርያም ጽፎታል