Get Mystery Box with random crypto!

በአማራ ክልል የ2015 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 23 - ጳጉሜ 04 ይካሄዳል። | Ethio University

በአማራ ክልል የ2015 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 23 - ጳጉሜ 04 ይካሄዳል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2015 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። በዚህም በ2015 የትምህርት ዘመን ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢሮው ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል።

ከነሐሴ 23/2014 ዓ.ም እስከ ጷጉሜን 04/2014 ዓ.ም ድረስ ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን የጠቆሙት የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን፤ በዚኽም 895 ሺህ 404 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች እንደሚመዘገቡ ገልጸዋል።

እድሜያቸው 7 ዓመት የሞላቸው ተማሪዎች 714 ሺህ 518 ተማሪዎች እንደሚመዘገቡም አስረድተዋል። በአጠቃላይ 745 ሺህ 708 የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች እንደሚመዘገቡ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አንስተዋል።

በአጠቃላይ 4 ሚሊዮን 144 ሺህ 845 ተማሪዎች በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲኹም 1 ሚሊዮን 219 ሺህ 301 ተማሪዎች በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚመዘገቡ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

ምዝገባው አዲስ ተማሪዎችን ብቻ ሳይኾን በተለያየ ጊዜ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎችን የሚያካትት እንደኾነ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል። በ2014 ዓ.ም 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋልም ነው የተባለው። (አሚኮ)