Get Mystery Box with random crypto!

ኤሎን መስክ ከ44 ቢሊዮን ዶላር የትዊተር ግዢ ስምምነት እራሱን አገለለ የዓለማችን ቁጥር አን | ኢትዮ ቴክኖሎጂ ( Ethio technology )

ኤሎን መስክ ከ44 ቢሊዮን ዶላር የትዊተር ግዢ ስምምነት እራሱን አገለለ

የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤሎን መስክ በርካታ የግዢ ስምምነቶች አልተከበሩም በማለት በ44 ቢሊዮን ዶላር ትዊተርን ለመግዛት ደርሶት ከነበረው ስምምነት እራሱን እያገለለ መሆኑ ተገለጸ።

ከሁለት ወራት በፊት የትዊተር ቦርድ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኩን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለኤሎን መስክ ለመሸጥ ተስማምቶ ነበር።

መስክ ከትዊተር ግዢ ራሱን ያገለለው የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያው ሐሰተኛ የሆኑ የትዊተር አካውንቶች ምን ያህል እንደሆኑ በቂ መረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው ብሏል።

ትዊተር በበኩሉ የግዢ ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ሕጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ አማራጮችን እያጤንኩ ነው ብሏል።

“የትዊተር ቦርድ ከመስክ ጋር በተደረሰው ዋጋ እና ደንቦች መሠረት ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት አለው” ሲሉ የትዊተር ቦርድ ሰብሳቢ ብሬት ቴይለር በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

በፎርብስ መጽሔት መረጃ መሠረት 273.6 ቢሊዮን የሚገመት የተጣራ ሃብት ያለው ኤሎን መስክ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ነው።

ይህም በዋነኝነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች በሆነው ቴስላ ውስጥ ባለው ድርሻ እና ስፔስ ኤክስ የተባለውን የህዋ በረራ ፕሮግራም ተቋም በኩል በሚያገኘው ገቢ ነው።

መስክ ትዊተርን ለመግዛት ከስምምነት መድረሱ በተገለጸበት ወቅት፤ የማኅበራዊ ትስስር መድረኩን ደንብ እና የአጠቃቀም መመሪያዎችን በማላለት ሰዎች በተሻለ ነጻነት እና አነስተኛ ገደብ ሃሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ ይፈቀዳሉ ግምቶች በስፋት ተነስተው ነበር።

“ነፃ ንግግር የዲሞክራሲ መሠረት ነው፤ ትዊተር ደግሞ ለሰው ልጅ የወደፊት ሕይወት ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ክርክር የሚደረግበት የዲጂታል አደባባይ ነው” ሲል ኤሎን መስክ ስምምነቱን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ገልጾ ነበር።

ትዊትር የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከማኅበራዊ መድረኩ ማገዱን መስክ አጥብቆ ተቃውሞ ነበር።

ሐሰተኛ አካውንቶች

መስክ ግንቦት ወር ላይ ‘ስፓም’ እና ሐሰተኛ የሆኑ አካውንቶችን በተመለከተ መረጃ እስኪገኝ ድረስ የግዢው ስምምነት “ባለበት እንዲቆም” ተደርጓል ብሎ ነበር።

ትዊተር ከአጠቃላይ ተጠቃሚዎቹ የሐተሰኛ አካውንቶች ቁጥር ከ5 በመቶ ያልዘለለ ነው ቢልም፣ መስክ ግን ማረጋገጫ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ቆይቷል። መስክ ይህ ቁጥር ከ20 በመቶ ያለነሰ ነው ብሎ ያምናል።

የኤሎን መስክ ጠበቆች ትዊተር ይህን ማረጋገጫ ማቅረብ አልቻለም ይላሉ።

ስፓም አካውንቶች አንድ ተመሳሳይ የሆነ መረጃ ያለ ተቀባዩ ፍቃድ እና እውቅና ለበርካታ ሰዎች የሚልኩ አካውንቶች ሲሆኑ፣ ሐሰተኛ አካውንቶች ደግሞ ትክክለኛ ባለሆነ ማንነት የሚከፈቱ አካውንቶች ናቸው።

ሐሙስ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም. ትዊትር በየቀኑ መሰል 1 ሚሊዮን አካውንቶች አስወግዳለሁ ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።