Get Mystery Box with random crypto!

ፈጠራ ወደ ከፍታ በሚያስፈነጥሩ ብዙ ችግሮች የተከበበ ነው ፤ መፍትሔ ተኮር ከሆንን ወደ መልካም አ | TVT institute

ፈጠራ ወደ ከፍታ በሚያስፈነጥሩ ብዙ ችግሮች የተከበበ ነው ፤ መፍትሔ ተኮር ከሆንን ወደ መልካም አጋጣሚ ልንለውጠው እንችላለን።

ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

3ተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር፣ “ክህሎት ለተወዳዳሪነት” በሚል መሪ  ሀሳብ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አቢይ አህመድ(ዶ/ር)፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ  ሀገራችን ብዙ ችግሮች እንዳሉበባቸውና አንዱ ዘርፍ የሌላው ግብዓት ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ የተሳሰሩ ባለመሆናቸውና በሚፈለገው ጥራት ስለማይመረቱ ከውጭ እንደሚገቡ በማስታወስ የክህሎት ውድድሩ ይህንን ለማስቀረት እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለማግኘት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ፈጠራ ወደ ከፍታ በሚያስፈነጥሩ ብዙ ችግሮች የተከበበ ነው ፤ መፍትሔ ተኮር ከሆንን ወደ መልካም አጋጣሚ ልንለውጠው እንችላለን።

የፋይናንስ፣ የቢሮክራሲ እና የመስሪያ ቦታ ችግርን የፈጠራ ሰዎች ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ሆኖም መፍትሔ ተኮር መሆንን ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

ውጤት ላይ ማትኮር ማለት በቀለለ ነገር አስቸጋሪ ነገርን ማለፍ መቻል ነው፤ ለዚህም የፈጠራን አስቸጋሪነት በመረዳት ፈተናዎች እንዳያቆሙን በተባበረ እና በተደመረ አቅም ኢንዱስትሪያችንን እናልማ ያሉት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ፈተና እና ችግርን ለማለፍ እንበርታ፣ እንፍጠር ፣ እንጠንክር ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ አንድ ዓመት ተኩል ቢሆነውም ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ማሳየቱን እና በውድድሩ መክፈቻ ሥነ ስርዓት የፈጠራ ሥራቸውን ይዘው የቀረቡት የፈጠራ ባለሙያዎች ለችግር ያስቀመጡትን መፍትሔ በውድድር መማማሪያ እና ያለንን ብቃት ማሳያ ነው ብለዋል።


የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው
ባስተላለፉት መልዕክት የክህሎት ልማት ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት የሚረጋገጥበት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡

በክህሎት የበቁ፣ ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ የአገራችን ብልፅግና  ዕውን እንዲሆን የራሳቸውን አስተዋፅኦ የሚበረክቱ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎችን በመጠቀም ለማፍራት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተተገበሩ ነው ብለዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ‹‹ከሥልጠና በላይ›› በሚል መርህ የክህሎት ልማት ልህቀትን ለማረጋገጥ በሚተገብራቸው  የሪፎርም ሥራዎች መካከል ገበያ መርና የመልማት ፀጋን በመጠቀም የስልጠና ማዕከላትን በዞን ማደራጀት አንዱ ስትራቴጂ መሆኑን የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትሯ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የማምረቻ ማዕከላት በማድረግ ተግባራዊ ውጤትን የሚያረጋግጡበት ሥርዓት በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

የክህሎት ልማት የዕድገት ምንጭ መሆኑን በማስገንዘብ ለዘርፉ በቂ ትኩረት እንዲሰጠው ለማስቻል ብዙ ርቀትን መጓዝ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን መስራት ይጠይቃል ያሉት ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት በአገር ዓቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ መሰል ውድድሮች የዘርፉን ገፅታ በመገንባትና ወጣቶች ዘርፉን ምርጫቸው እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም አመልክተዋል፡፡

ከኮሌጆች ጀምሮ በተካሄዱ ውድድሮች ሦስት ምዕራፎችን አልፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የበቁ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ተወዳዳሪዎችን ያካተተው 3ኛው አገር አቀፍ የክህሎት ውድድር የቴክኖሎጂ ሽግግርን ዕውን ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የክህሎት ውድድር ላይ ለመሳተፍና የዓለም ዓቀፉ የክህሎት ማህበረሰብ (skill society) አባል  ለመሆን ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባና ተገቢውን መስፈርት አሟልታ ምላሽ እየተጠባበቀች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡

የክህሎት ልማት ዘርፍ ተጠናክሮ እንዲወጣ አደረጃጀቱን በመከለስና የነበረውን የፖሊሲ ማነቆ በመፍታት ረገድ የኢፌድሪ መንግስት ላሳየው ቁርጠኝነትም ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

ግንቦት 14/2015 ዓ.ም፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፡