Get Mystery Box with random crypto!

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅ ዱስ ስም የተወደዳቹ የዚህ ጹሑፍ ቤተሰቦች እንኳን | Ethiopian Orthodoxs Daily

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅ ዱስ ስም የተወደዳቹ የዚህ ጹሑፍ ቤተሰቦች እንኳን አደረሳችሁ ሰባኤውን በሰላም አስፈጽሞ ለዚህ ታላቅ ቀን ያደረሰን አምላክ ይክበር ይመስገን።

የዛሬን መልዕክት ከብዙ በጥቂቱ በሦስት ክፍል ከፍዬ አቅርቢዋለሁና በረከቷ ረድኤቷ ይድረሰን አሜን!

ነሐሴ 16 በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ::

ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር::

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው::

ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር 16 ቀን ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ::

የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው::

የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው::

እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት::

ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ::

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ::

ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፅዋት ሁሉ አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት::

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት::

በኪሮቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጅዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች::

2...ወንጌላዌ ዮሐንስ ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ወረደ።

ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽመው ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው::

እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንዳሳረጓት ነገራቸው::

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ::

ከዚህ በኋላ እያዘኑ ሳለ እንሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላቹ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ::

እንሆ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ::

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴ ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን::

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉኑም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዶ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት::

እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እየአንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው::

የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዔ ካህን ሆነ::

እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ::

ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሁኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ::

3.....ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋ ውንና ደሙን አቀበላቸው::

ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት::

በዚህች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው::

መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚህች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ::

የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርጉ ሁሉ በዚህች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውቱ ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው::

እመቤታችንም ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው።

ልጄ ሆይ እንሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸው ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ድንቆች ሥራዋችን አዩ::

እመቤታችንም ይህንን ስትናገር በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ::

የተወደዳቹ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለ እኛ ወደተወደደ ልጅዋ ሁል ጊዜ ትማልዳለችና::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን በረከቷም ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን::
@ethiopianorthodoxs