2022-07-19 09:20:57
ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ስምምነቱ እዲጸድቅ ሲወስን ከላይ የተገለጹ ስምምነቱ እና ማብራሪያው እንዲሁም ረቂቁን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 11 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ስምምነቱን ከተቀበለው የማጽደቂያ አዋጅ ያወጣል።
ሀገራት በአንድ ስምምነት ላይ የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ተዓቅቦ (reservation) ማድረግ የሚችሉ ሲሆን በማፅደቅ ሂደቱ ይህ ካለ ማጽደቂያው ይሄንኑ ማካተት አለበት፡፡ በዚህ ሂደት ያለፈ አለምአቀፍ ስምምነት የሀገራችን ህግ አካል ይሆናል፡፡
ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግ ምንድን ነው?
ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግጋት የሚባሉት ከመደበኛው እና ከተፃፈው ስምምነት ወይም ቃልኪዳኖች የሚመነጩ ሳይሆን ከሀገራት አለምአቀፍ ተግባርና ልማድ የሚመነጩ ህግጋት ሆነው ሀገራት በተደጋጋሚነት እና በተከታታይነት ሲተገብሯቸው የቆዩ ጠቅላላ ተግባራዊ ልምዶች (general state practices) እና ሀገራቱ እነዚህኑ እየተገበሯቸው ያሉት ልምዶች እንደ አስገዳጅ ህግ ተቀብለዋቸው (opinio juris) ከሆነ እንደ ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት በሀገራት አለምአቀፍ ግንኙነት ውስጥ አንድን ግዴታ ወይም መብትን በመቀበል በተደጋጋሚ ተመሳሳይ አቋምና ተግባር ካለ ወደፊት በዚህ ጉዳይ የዚህ ሀገር መብት ወይም ግዴታ ምንድነው ሲባል ይህው ልማድ እንደሆነ ይወሰዳል ማለት ነው፡፡ ይህ የሀገር አቋምና ተግባር በሀገር መሪ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በሚመለከተው ሚኒስተር፣ አምባሳደር ንግግርና ተግባር ወይም ከሀገሪቱ ተቋማት ወይም ፍርድ ቤት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሀገራትን ወክለው በአለምአቀፍ መድረክ በወከላቸው ሀገር ስም የሚያደርጓቸው ንግግሮች፣ የሚይዝዋቸው አቋሞች ተደጋግመው እና እንደ አለምአቀፍ ግዴታ ሲወሰዱ ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግ ሆነው ወደፊት በሚነሱ መሰል ጉዳዮች ላይም አስገዳጅ ተፈታሚነት ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን (ዓባይ) በፍትሀዊነት መጠቀም እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን አለማቀፍ ድንበር ውዝግብ በተመለከተ ሀገራችን በተወካዮች በኩል በአለምአቀፍ መድረክ የምትይዘው አቋም እንደ ልማዳዊ ህግ እያደገ ስለሚሄድ የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ያስጠበቀ ወጥነት ያለው እና የማይናወጽ አቋም ይዞ ጉዳዩን መከታተል ያስፈልጋል፡፡
በስምምነት ህግ ከተጻፉ ጉዳዮች የተወሰኑ ጉዳዮች በአለምአቀፍ ደረጃ ሙሉ ስምምነት በሚያስብል ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸው እንደ አስገዳጅ ህግ ሀገራት በራሳቸው ፍላጎት የሚተገብሯቸው ሲሆን እነዚህ ጉዳዮች የሚታዩበት አግባብ ከፍ ወደሚል ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግነት አድጓል፡፡ ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት ስምምነቶች በክልከላነት የተደነገጉ ሰውን ማሰቃየት፣ እንደ ሰው እውቅና አለመስጠት እና በባርነት አለመያዝ፣ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ አለመገደል፣ በአራቱ የጄኔቫ ስምምነቶች የተደነገጉ የጦርነት ወይም የሰብአዊነት ህግጋት ውስጥ የተካተቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ወደ ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግነት ደረጃ ያደጉ ልምዶች (አለምአቀፍ ግዴታዎች) ተደርገው ይወሰዳሉ (jus cogens)፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የእኛም ሀገር ህግ አካል ሲሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገመንግስት፣ የወንጀል ህግ እና ሌሎች ህግጋቶቻችን ውስጥ በስፋት የተደነገጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ስለ ጠቅላላ የህግ መርሆች
ጠቅላላ የህግ መርሆች የሚባሉት በዲሞክራሲ ስርአት ውስጥ በሂደት የዳበሩ እና በየሀገራቱ የህግ ስርአት ተግባራዊ የሚደረጉ ሆነው በዚህም አለምአቀፍ ተቀባይነት ያገኙ መርሆች ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆች በአለምአቀፍ ግንኙነት እና ክርክር አፈታት ሂደት ላይ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ የህግ መርሆች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ውል የገባ በውሉ የተጣለበትን ግዴታ እንዲያከብር “ቃሉ ማሰሪያው ነው” (Pacta sunt servanda)፣ በአገራት ግንኙነት ሂደት የቅን ልቦናን መርህ (good faith) መከተል የሚሉ እና መሰል መርሆች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ መርሆቹ በአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን ስፋት ባለው መልኩ በተለያዩ ሀገራት የህግ ስርአት የዳበሩ መርሆዎች መሆን አለባቸው፡፡
የትኞቹ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ናቸው በአለምአቀፍ ህግ ምንጭነት የሚወሰዱት?
በአለምአቀፍ ህግ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ አዲስ ለሚታዩ ጉዳዮች እንደ መርህ መጠቀም የማይፈቀድ መሆኑን ከአለምአቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት (ICJ statute) አንቀጽ 59 መረዳት ይቻላል፡፡ በዚሁ ስምምነት መሰረት የውሳኔው ተፈጻሚነት በተከራካሪ ወጎኖች ላይ ብቻ መሆኑን ደንግጓል፡፡ ነገር ግን ከአለምአቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት (ICJ) እና ሌሎች አለምአቀፍ ፍርድ ቤቶች ተፈጻሚነት ያለውን አለምአቀፍ ህግ ለመለየት የራሳቸውን ያለፈ ውሳኔ ተመልሰው የሚያዩበት አሰራር ያለ በመሆኑ አለምአቀፍ ህግ ምንጭነት የፍርድ ቤት ውሳኔን ማግለል የሚቻል አይደለም፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም በተሰጠ ውሳኔ የአንድ አለምአቀፍ ስምምነት ወይም የአንድ ግዴታ መኖር አለመኖር በምን መልኩ እንደተተረጎመ በማጣቀስ የአለምአቀፍ ህግን ለመለየት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የየትኛው ፍርድ ቤት? የአለምአቀፉ ወይስ ሀገራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ? ለሚለው ጥያቄ ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው፡፡ አለምአቀፉ ፍርድ ቤት ከላይ ባነሳነው መልኩ የሚተገበር ሲሆን ሀገራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔም ሀገራት አንድን አለምአቀፍ ግዴታ የሚጥልን ጉዳይ ከዚህ በፊት የወሰኑበትን አግባብ በማየት ግዴታው በሀገራቱ የህግ ስርአት ያለ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ወይም ሀገራቱ ጉዳዩን ልማዳዊ አለምአቀፍ ህግ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ በአስረጅነት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በዚህ አግባብ ውሳኔዎች የአለምአቀፍ ህግ ምንጭ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
በአለማቀፍ ህግ የታወቁ ምሁራን ከሚያሳትሙት ጽሁፍ የሚገኙ አስተምህሮቶች እና ሌሎች በህጉ በግልፅ ያልተገለጹ ጉዳዮች ላይ ያሉ ትርጓሜዎችና ትንታኔዎች በማስረጃነት የሚታዩ መሰል ጉዳዮች እንደ ሁኔታው የሚያስፈልጉ እና በሁለተኛ ደረጃ በአለምአቀፍ ህግ ምንጭነት የሚገለጹ ናቸው።
የአለምአቀፍ ህግን ተፈጻሚነት ወሰን ያውቁ ኖሯል?
ዓለምአቀፍ ህግ እንደ የህጉ ምንጭ የአፈጻጸሙ ወሰንም የሚወሰን ነው፡፡ ከስምምነት የሚመነጭ አለምአቀፍ ህግ ተፈጻሚነቱ በፈራሚ ሀገራት ላይ ብቻ ሲሆን ፈርመውም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ተዓቅቦ ያሰሙ ፈራሚ ሀገራት በታቀቡበት ጉዳይ ላይ እንዲፈጸምባቸው አይገደዱም። ከልማዳዊ አለምአቀፍ ህግ ጋር በተገናኘም ከላይ እንዳነሳነው የተፈጻሚነት ወሰኑ የሚታወቀው የሀገራትን ጠቅላላ ልምድ እና እንደ ህግ ግዴታ ጉዳዩን መቀበላቸው ነው። በእያንዳንዱ ጉዳይ ከሀገር ሀገር ይለያያል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል እንዳነሳነው አንዳንድ አለምአቀፍ ግዴታዎች ጠቅላላ ግንዛቤ ተፈጥሮ በሁሉም ሀገራት እንደ ግዴታ የሚፈጸሙበት ሁኔታ በልማድ ሂደት ስለተፈጠረ እንደነዚህ አይነቶቹ አለምአቀፍ ግዴታዎች የተፈጻሚነታቸውን ወሰን በአለምአቀፍ ደረጃ ያደርገዋል፡፡
851 views06:20