Get Mystery Box with random crypto!

#የልብ_ነገር #ክፍል_ሶስት (ፉአድ ሙና) *** አየሁት እንባዋን ከመከፋቷ ውስጥ፣ ሲረግፍ እን | ጣፋጭ ታሪኮችና ወጎች

#የልብ_ነገር
#ክፍል_ሶስት
(ፉአድ ሙና)
***

አየሁት እንባዋን
ከመከፋቷ ውስጥ፣ ሲረግፍ እንደዝናብ
ምን ነበር ቢጠረግ፣ የመራቋ ነገር ከታሪካችን ባብ!

ሳቅ አየሁኝ ከዚህ
ሳቅ አየሁኝ ከዛ፣ የተመሳቀለ፣
አንዷ ትዝታዬን፣ እሷን የመሰለ።

***
ፌሪዬ ውጪ በሄደች በሁለተኛው ዓመት መጨረሻ ከባድ የሆነ መርዶ አረዳችኝ። የምትሰራበት ተቋም ውጪ ያለው ቢሯቸው ላይ ለሁለት ዓመት እንድትሰራ እንደጠየቋት ነገረችኝ።

ካፌ ውስጥ ተቀምጬ ነበር። ከፌሪ የተደወለልኝን የቪዲዮ ጥሪ አነሳሁ።

«እ ምን አሉሽ?» ፊቴ ላይ ቁጣዬ ይነበባል።
«አይቻልም አሉኝ!»
«ምን ማለት ነው?» ሳላስበው በጣም ጮህኩ። ቁጣዬን መቆጣጠር እየተሳነኝ ነው።
«የገባሽው ስምምነት ላይ ተካቷል .... የውል ግዴታሽን መፈፀም አለብሽ አሉ።»
«ታውቂ ነበር ፌሪ! ታውቂ ነበር! ከጅምሩ ከዚህ እንደማለቅሽ አስበሽ የዘየድሽው መላ ነው። ታውቂ ነበር! አትወጂኝም እንዴ? በግድ ነው እንዴ የተጋባነው?»
«ወላሂ አላውቅም ነበር ፋሚዬ! እንዴት እኔ ካንተ መሸሽ እፈልጋለሁ? አባቴ ደስ እንዲለው ነው እንጂ .... »  ማልቀስ ጀመረች።
«በለቅሶሽ ልታሳምኚኝ አትሞክሪ! አሁን ቲኬት ቆርጬ እልክልሻለሁ! ትመጫለሽ!» ስልኩን ጠረቀምኩባት!
ፀሀፊዬ ጋር ደውዬ ለፌሪ የመመለሻ ትኬት እንድትቆርጥ ነገርኳት። እንደ እብድ እያደረገኝ ነው። ካፌው ውስጥ ያለው ሰው በሙሉ ከንፈሩን እየመጠጠ ያየኛል።

ወደ ቢሮዬ ስመለስ ፌሪ ከሳምንት በኋላ የምትመለስበት የአየር ቲኬት ተቆርጦ ጠበቀኝ። ትኬቱን ፎቶ አንስቼ ለፌሪ ላኩት። ፌሪ ደጋግማ እየደወለች ነው .... አላነሳሁላትም። ወደ ቤት ሄጄ ሶስት ቀን ሙሉ ከቤት ሳልወጣ ቆየሁ። በሶስተኛው ቀን ፌሪ የምትልካቸው የድምፅ መልዕክቶች ስላሳዘኑኝ ደወልኩላት።

«የኔ ጌታ! አለቃዬ! ፍቅሬ!» ድምጿ አንጀት ይበላል።
«ምንድነው?»
«ትኬቱን እኮ አየሁት .... »
«እና!»
«አንተ ጌታዬ ነህ .... አስተዳዳሪዬ ነህ .... የበላዬ ነህ .... በህይወቴ ሁሉ ወሳኙ አንተ ነህ ፋሚዬ ...» ማልቀስ ጀመረች። በዝምታ ጠበቅኳት። ድምጿን ሳግ እየተናነቀው ቀጠለች።
«ነይ ካልክ .... ከወሰንክ እመጣለሁ። እስከዛሬ እንቅልፍ ሳልተኛ የለፋሁለትን ማስተርሴን ትቼው እመጣለሁ።»
ድምጿ ውስጥ እውነተኝነት አለ። በጣም ሲከፋት የምታወራበትን ድምፀት አውቀዋለሁ።
«አላውቅልሽም! ትምህርቱ ገደል መግባት ይችላል!» ልቤን መረበሿ ቢሰብረውም ለመጠንከር ሞከርኩ።
«ሁለት አመት ሙሉ ታግሰሀል እኮ አባ! ለሁለት አመት በናፍቆት የተሰቃየነው ሁሉ ገደል ይግባ የኔ አለቃ .... ጌታዬ!»
«ልትጨቃጨቂኝ ነው ካልደወልክ ያልሽው?» ስልኩን ዘጋሁባት።

ደጋግማ ደወለች። ትንሽ ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ አነሳሁት።

ፌሪዬ ከአይኗ እንባ እየተንዠቀዠቀ ነው። ፊቷ ረጥቧል። የበደልኳት ያህል ጨነቀኝ።

«እሺ የኔ ጌታ .... እመጣለሁ። ትዕዛዝህን አከብራለሁ የኔ ፍቅር! ምን ይዤልህ ልምጣ?» መንሰቅሰቅ ጀመረች።

«ምንም አልፈልግም!» ተሰነባብተን ስልኩ ተዘጋ።

ስልኩን እንደዘጋሁት ልቤ ደረቴን እንደአታሞ መደብደብ ጀመረ። ፈራሁ .... ጨነቀኝ .... በምድር ላይ የምሳሳላትን አንድ ፍጡር የበደልኳት መሰለኝ። ራሴን አረጋግቼ ውሳኔዬ ላይ ለመፅናት ሞከርኩ። ሰውነቴ መንቀጥቀጥ ጀመረ። ለቅሶዋ አይኔ ላይ እየተደቀነ ሰላም ነሳኝ። በረራዋ ሁለት ቀን ሲቀረው ደወልኩላት። ትልቅ የገበያ ማዕከል ውስጥ ነበረች።

«የኔ ፍቅር .... የኔ ፌሪ ...» ተንተባተብኩ።
«ወዬ ፋሚዬ» ፈገግ ለማለት ሞከረች።
«ምን እየሰራሽ ነው ሞል ውስጥ?»
«አንዳንድ ነገር Shop እያደረግኩ ነው። Gift ምናምን!»
«ለማን?»
«ለቤተሰብ .... For our dads and moms ምናምን!»
ማልቀስ አማረኝ .... ልቤን አንዳች ነገር እፍን አደረገኝ።
«ፌሪዬ .... »
«ወዬ ፍቅር»
«በጣም አፈቅርሻለሁ እሺ!»
«እኔ ደግሞ ካንተ በላይ!»
«በቃ ጨርሰሽ ነይ እሺ .... ፈቅጄያለሁ።»
«ማለት?»
«በቃ እንዲከፋሽ ... በእኔ ምክንያት ልፋትሽም ገደል እንዲገባ አልፈልግም! እንግዲህ እንደምንም እችለዋለሁ። ጨርሺና ከማስተርስሽ እና ከስራ እድገትሽ ጋር ደስ እያለሽ ተመለሽ።»
ተንሰቀሰቀች .... ባለችበት ተንበርክካ ተርገፈገፈች።
«በቃ አታልቅሺ የኔ ውብ .... አታልቅሺያ!»
«እወድሀለሁ ፋሚዬ .... ወላሂ እወድሀለሁ የኔ ጌታ! እንደማትጨክንብኝ አውቅ ነበር። የኔ ንጉስ!»
«አሁን ስትስቂ ማየት ነው የምፈልገው!»
ጥርሶቿ ፈነጠቁ። ፈገግታዋ እና የአይኗ ጨረር .... ደካማ ጎኖቼ ተለቀቁ። ደረቅ መሬት ላይ የመጀመሪያዎቹ የዝናብ ጠብታዎች የሚያስነሱት አይነት አብዋራ .... ከልቤ ላይ በፈገግታዋ ተጠረገ። የመታፈኔ ስሜት ለቀቀኝ። ፌሪዬ ሳቀች። ፌሪዬን ደስ አላት። በተጨማሪ ሁለት አመታት ስቃዬ ፈገግታዋን .... ሳቋን ገዛሁላት።

***
«ፉአድ ሙና?»
«አዎ!»
«የምር ስምህ ነው? ማለቴ ሙና?»
የቢሮዬ እንግዳ መቀበያ ላይ አንድ የቋሚ ደንበኛችን ልጅ አዲስ ስለጀመረችው ቢዝነስ እያማከረችኝ ነው። ሰሞኑን በየሁለት እና ሶስት ቀኑ ትመላለሳለች።
«የሚጠጣ ምን ይምጣልሽ?»
«ኧረ ደስ አይልም ፉዬ! እንደባለፈው ልታረሳሳኝ ነው አይደል?»
«ምኑን?»
«ሙና የሚለውን ነዋ!»
«ቆይ ስሜን ልታጠኚ ነው እንዴ የምትመጪው?»
«አይደለም!»
«እኮ ስለ ስራሽ ብናወራ ይሻላላ!»
«ስራውን ብዬ አይደለም የምመጣው ጓደኛሞች እንደሆንን አስቤ ነው። ጓደኛሞች ሆነናል ተባብለን የለ እንዴ ባለፈው?»
«አዎ ልክነሽ!» እንዳለችኝም ሆነ እንዳልኳት ምንም አላስታሰውስም። ግን ላስከፋት አልፈለግኩም።
«ስለ ስራው እኮ በቃ የምፈልገውን ነግረኸኛል። ካንተ ቢዝነስ ጋር የማይገናኘውን ደግሞ አንድ ዘመዳችን አለች ከሷ ጋር አውርተናል። እንዳንተ አይነት ጓደኛ ስለፈለግኩ ነው። ባትኮራብኝ ነው የሚሻልህ!»
ቅብጠቷ ትንሽ ስላሰጋኝ ሰራተኛዎቼ እንዲሰሙን አልፈለግኩም። ወደ ቢሮዬ ይዣት ሄድኩ።
«እሺ ልጅ ኢክራም!»
«ምነው የአባቴን እና የአያቴን ተውከው?»
«ኢክራም ባርጊቾ ነስሩ!»
«ስርዓታ!»
«እሺ በቃ! ኢክሩ ጓደኛዬ .... ለምን ምሳ አልጋብዝሽም?»
ተፍለቀለቀች። በጣም ደስ እያላት ከመቀመጫዋ ተነሳች።
«ስማ ግን ምሳ እየበላን ትነግረኛለሀ? ስለ ሙና!»
«ችግር የለውም እነግርሻለሁ!»

ምሳ ለመብላት ከቢሯችን አቅራቢያ ወዳለ አንድ ታዋቂ ሆቴል ሄድን። ወደ ሆቴሉ ስንገባ ኢክራም እየሳቀች «ስማ ምሳ አበላሻለሁ ነው አይደል ያልከኝ?» አለች።
«ሬስቶራንት አላቸው ውስጥ!»
«እ እኔ ደግሞ room ብቻ መስሎኝ!» ትስቃለች።
«ተጫዋች ነሽ!»
«ተጫዋች ሰው አትወድም?»
«ኧረ እወዳለሁ።»
«ስለዚህ ትወደኛለሀ!» ትስቃለች።
«ፐ ሎጂክ!» ወንበር ስቤ አስቀመጥኳት!
«ፐ ደግሞ Romantic ነሽ!»
«ሚስት ስላለኝ አይጠፋኝም!»
«እና ለእሷ እንደምትስበው ነው የሳብክልኝ?»
«ለሷ አልስብላትም!»
«ለምን?»
«ሁሌ ታፋዬ ላይ ነው የምትቀመጠው!»
«እንደዚህ ሬስቶራንት ስትበሉም?»
«ሬስቶራንት ውስጥ አንበላም!»
«እና!»
«ቀልዴን ነው ባክሽ!» መውጫ ስታሳጣኝ መሸነፍ መረጥኩ።
«ለማንኛው አሳሳብ ላይ ጎበዝ ነህ! ከዚህ በኋላ አንተ ካልሳብክልኝ አልቀመጥም!»
«ቆመሽ ትቀሪያለሻ!»