Get Mystery Box with random crypto!

የቆዳ በሽታ ምርመራ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች ሀገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክ | Ethiopian Artificial Intelligence Institute

የቆዳ በሽታ ምርመራ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች

ሀገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጫና ከሚፈጥሩ ለሞት የማይዳርጉ በሽታዎች መካከል የቆዳ በሽታ ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህን የተረዳው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ፒክሽን ሄልዝ የተባለ ጀማሪ ተቋም በማሽን ለርኒንግ እና ኮምፒዩተር ቪዥን የሚታገዝ የቆዳ በሽታ መመርመሪያ መተግበሪያ አስተዋውቋል፡፡

መተግበሪያው የሕክምና ባለሞያዎች የቆዳ በሽታዎችን በቀላሉ ፎቶ በማንሳት የበሽታውን ምንነት ለመለየት እንዲያስችላቸው በማለም መበልፀጉ ተመላክቷል፡፡

መተግበሪያውን ለማበልፀግ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቆዳ ሐኪሞች (ደርማቶሎጂስት) መሣተፋቸው ተገልጿል፡፡ በውጤቱም ከአስራ ስምንት ሀገራት የተውጣጣ የቆዳ በሽታዎችን የሚያመለክት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የፎቶ ስብስቦች መተግበሪያውን ለማስተማር መዋላቸውን መረጃው አመላክቷል፡፡

በተቋሙ መረጃ መሠረት በዓለማችን ላይ በየዓመቱ 2.3 ቢሊዮን ሰዎች ለቆዳ በሽታዎች መፍትሔን በመሻት ወደ ጤና ተቋማት ይሄዳሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ ሁለት ሦስተኛው በዘርፉ ስፔሻሊስት ባልሆኑ ባለሞያዎች ሕክምና የሚደረግላቸው ሲሆን፤ ሃምሳ በመቶዎቹም ለተሳሳተ ምርመራ ተጋላጭ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም በዘርፉ የሠለጠኑ ስፔሻሊስቶች ከአንድ መቶ ሰባ እንደማይዘሉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህም በሀገራችን የጤና ተቋማት ላይ የሚፈጥረውን ጫና የተረዳው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሀገራችን የሚከሰቱ የቆዳ በሽታዎችን መለየት የሚችል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓት አበልፅጎ ወደ ስራ ለማስገባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡