Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ ፴ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሰኔ ሠላሳ በዚህች ዕለት ነቢይ ሰማዕትና ሐዋርያ የሆነ መጥምቁ ዮሐ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ሰኔ ፴
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ


ሰኔ ሠላሳ በዚህች ዕለት ነቢይ ሰማዕትና ሐዋርያ የሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ተወለደ። ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው። ይህም በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች። ዘመዶቿና ጐረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለርስዋ ደስ አላቸው።

በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን አይሆንም ዮሐንስ ይባል አለች። ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም አሏት። አባቱንም ጠቅሰው ማን ሊባል ትወዳለህ አሉት። እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም 'የልዑል ነቢይ' እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።

ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሔዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት እንዲገድሉትም ጭፍሮችን ላከ ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋራ እንዲሔዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።

ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው። ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት። ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ኖረ።

"የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ ጥርጊያውንም አስተካክሉ" እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እነሆ ብሎ ኢሳይያስ የተናገረለት ይህ ነው። ሚልክያስም ስለሱ እንዲህ አለ። "በፊትህ ጐዳናዬን አስተካክሎ የሚጠርግ መልእክተኛዬን እኔ እሰዳለሁ።'

ራሱ መድኃኒታችንም ስለርሱ ሲናገር "ሴቶች ከወለዱአቸው መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጠው የለም" ብሏል። ይህ የእግዚአብሔርን ልጅ በአጠመቀውና የማትዳሠሥ ራሱን በዳሠሠው ጊዜ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል የአብን ቃል ሰምቷልና።

ዳግመኛም ክብር ይግባውና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥ አየ። እኛም መድኃኒታችን እንዲምረንና ይቅር እንዲለን በአማላጅነቱ እያመን መታሰቢያውን እናድርግ፡፡

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox